በሐረሪ ክልል የስራ እድል ለመፍጠርና የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት አመራሩ ቅንጅቱን አጠናክሮ መስራት እንዳለበት ተጠቆመ

ሐረር፣ ግንቦት 24/2015 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የስራ እድል ለመፍጠርና የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት አመራሩ ቅንጅቱን አጠናክሮ ሊሰራ እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱልጀባር መሀመድ አስገነዘቡ።

በክልሉ በምግብና ሸቀጦች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋትና ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር ለማስቻል ያለመ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱልጀባር መሀመድ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሸቀጥ ዋጋን ለማረጋጋት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ፓርቲው በክልሉ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተካተቱበት ግብረ ሃይል በማቋቋም የግብርና ምርቶችን ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በማምጣት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲዳረስ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በክልሉ ዋጋን ለማረጋጋት እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም ቀጣይነት ያለው ስራ ማከናወን ተገቢ መሆኑን አስምረውበታል።

በተለይ የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት በሚከናወኑ ስራዎች ላይ ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን ከመቅረፍ አንጻር አሁንም ክፍተት እንደሚታይ ጠቁመው፤ ችግሮቹን ለመቅረፍ አመራሩ ተቀናጅቶ መስራት አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል።

አቶ አብዱልጀባር አክለውም፤ በክልሉ በቀጣይ አምስት ወራት በሚከናወነው ንቅናቄ አመራሩ ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጎልበት ወጣቱን  የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ለስራ እድል ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን በባለቤትነት በመቅረፍና የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በክልሉ በሚገኙ ገጠር ወረዳዎች ላይ ወጣቱን በግብርና ዘርፍ በማሰማራት አምራችነት እንዲጎለብት የማድረግ ስራ መጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የክልሉ ንግድ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቡሽራ አልይ በበኩላቸው በክልሉ አነስተኛና ቋሚ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ዘንድሮ በቅዳሜ ገበያ  30 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የግብርና ምርት ግብይት እንዲከናወን ተደርጓል ብለዋል።

በተጨማሪም 696 ሺህ ሊትር ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲከፋፈል መደረጉን ተናግረዋል።

ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 1 ሺህ 452 ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

በቀጣይ አምስት ወራትም በክልሉ ነጻ የምርት ዝውውርን በማጎልበት፣ በቂ የምርትና የሸቀጥ አቅርቦትን በማሳደግ፣ ህገ ወጥ ነጋዴዎችንና ደላላዎችን በመከላከል ዋጋ የማረጋጋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የክልሉ የኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አሪፍ መሀመድ በቀጣይ አምስት ወራት ከሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በተቀናጀ ለዜጎች የስራ እድል የመፍጠር ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በቀጣይ አምስት ወራት በግብርናና አረንጓዴ አሻራ ልማት 2 ሺህ 600 ወጣቶችን ስራ ለማስያዝ መታቀዱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም