ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ከ109 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል - የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ - ኢዜአ አማርኛ
ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ከ109 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል - የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ
አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015(ኢዜአ)፦ በጉራጌ ዞን ለአምስተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ109 ሚሊየን በላይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ ለኢዜአ እንዳሉት ለግብርና ምርታማነት በተሰጠው ትኩረት በበጋ መስኖ ስንዴና በመደበኛ የመኸር ሰብል ልማት ውጤታማ የምርት አሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በመደበኛ መስኖ ልማት ስራም ከ52 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በማከናወን 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ14 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
በመደበኛ የመስኖ ልማት የተቀመጠውን ግብ ከዕቅድ በላይ በማሳካት እንደ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ካሮት፣ ሽንኩርት ሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ዓይነቶችን ማልማት መቻሉንና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዞኑ የምርታማነት ልማት ስራ እየተሻሻለ መምጣቱን አመልክተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ወራትም ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት የበጋ መስኖ ስንዴን በማልማት እስካሁን ከ80 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ እንደተቻለ ጠቁመዋል።
ለአምስተኛው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ-ግብር ቅድመ ዝግጅትም እንደዞን ከ109 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ-ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኝ መዘጋጀታቸውንና ከዚህም ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚገኝበት ነው አቶ አበራ ያስረዱት።
የፍራፍሬ እጽዋቶችን ማልማት የአርሶ አደሩን የምግብ ፍጆታ በማረጋገጥ የገበያ አማራጭ መፍጠር እንደሚያስችል አመልክተዋል።
ለመርሐ-ግብሩ ከ18 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተያዘው አምስተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውን በመጠቆም፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን በብዛት እንደሚተከሉ ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው።