በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ውጤታማ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሁሉም ጥረት ሊታከልበት ይገባል- ዶክተር ፍጹም አሰፋ

362

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015 (ኢዜአ) በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ውጤታማ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሁሉም ጥረት ሊታከልበት ይገባል ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።  

የግብርና ሳይንስ ኤግዚቢሽን ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ለጎብኝዎች ክፍት መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም እስካሁን የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሌሎችም ኤግዚቢሽኑን ጎብኝተዋል። 

በዛሬው እለትም የፌደራልና የክልል የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አውደ-ርዕዩን ጎብኝተዋል።


 

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የገንዘብ  ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፣ የፕላንና  ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የደቡብ  ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እና ሌሎችም የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ከጉብኝቱ ጎን ለጎንም በሲዳማ  እና ደቡብ  ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የተዘጋጀውና በሌማት ትሩፋት የተገኙ ውጤቶችን የሚያስቃኝ አውደ-ርዕይን በሳይንስ ሙዚየም መርቀው ከፍተዋል።

በሁለቱ ክልሎች የተዘጋጀው አውደ-ርዕይ ላይ የዓሳ፣ የማር፤ የአትክልትና  ፍራፍሬ፣ የቅመማቅመም፣ የእንስሳት ተዋጽዖዎችን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ውጤቶች ለዕይታ ቀርበዋል። 

በኢትዮጵያ በሌማት ትሩፋት፣ በስንዴና የአረንጓዴ ልማት መርሃ-ግብሮች ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገልጸዋል።   

በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ እያደገ የመጣው የግብርና ሜካናይዜሽን ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆኗን በተግባር እያየን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ለዘመናት ከውጭ ይገባ የነበረውን ምርት በማስቀረት ለውጭ ገበያ ጭምር ማቅረቧ የውጤታማነቱ ሁነኛ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ውጤታማ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሁሉም ጥረት ሊታከልበት ይገባል ብለዋል።    

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፤ የግብርና ሳይንስ አውደ-ርዕይ የግብርናው ዘርፍ በእውቀትና በቴክኖሎጂ ከተመራ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።  


 

በክልሉ በተለይም በቡና፣ ሰሊጥ፣ ቅመማቅመም፣ ማርና የእንስሳት ተዋጽኦ ሰፊ ኃብት መኖሩን ጠቅሰው፤ በአግባቡ ማልማት ከተቻለ አገር መለወጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በሁሉም አካባቢዎች ኢትዮጵያ ኃብቷን ማልማት ከቻለች እድገትና ብልጽግናዋን በአጭር ጊዜ ማሳካት ያስችላልም ነው ያሉት።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ በግብርናው መስክ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ለአገር እድገትና ለዜጎች የኑሮ መሻሻል ትልቅ ተስፋ የሰነቀ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በሲዳማ ከክልል ባለፈ ለአገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚያስችል እምቅ ኃብት በመኖሩ የልማት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው፤ የግብርና ሳይንስ አውደ-ርዕይን እስካሁን ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች የጎበኙት መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣዩ እሑድ የሚጠናቀቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

አውደ-ርዕዩ የግብርናውን ዘርፍ የሚያጠናክር ትልቅ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ገልጸው፤ የጎብኝዎችም ፍላጎትና ተነሳሽነት ከተገመተው በላይ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በግብርና ሚኒስቴር፣ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና ኢትዮ-ቴሌኮም በጋራ የተዘጋጀው የግብርና ሳይንስ አውደ-ርዕይ የግብርናው ዘርፍ ያለበትን ደረጃ የሚያሳዩ ምርቶች፣ የግብርና  ቴክኖሎጂዎች እና የምርምር ውጤቶች ቀርበውበታል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም