በሀዋሳና ጅማ አዲስ የደረቅ ወደብ ተርሚናል ግንባታ በቅርቡ ይጀመራል - የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ

233

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015(ኢዜአ)፦በሀዋሳና በጅማ አዲስ የደረቅ ወደብ ተርሚናል ግንባታ ሂደቶች በቅርቡ የሚጀመሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የወደብና ተርሚናል ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምሕረተአብ ተክሉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በአገሪቱ ለገቢና ወጪ ጭነቶች የሎጂስቲክስ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

የወጪና ገቢ ንግድ ፍሰት የሚመጥንና ሊያስተናግድ የሚችል የሎጂስቲክስ አቅርቦትና የደረቅ ወደብ ተርሚናል ማስፋፊያ እንዲሁም አዳዲስ የደረቅ ወደብ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም ተጨማሪ የደረቅ ወደብ ግንባታ በየጊዜው እየጨመረ ሲሄድ የወጪ ገቢ ንግድ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሃብቶችን ለማበረታታትና ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር የላቀ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

በመሆኑም ተቋሙ በሀዋሳና በጅማ ሁለት አዳዲስ የደረቅ ወደብ ተርሚናሎች ግንባታን በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚጀምር ጠቅሰው፤ ለፕሮጀክቶቹ ቅድመ ግንባታ ለእያንዳንዳቸው 150 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞላቸዋል ነው ያሉት።

ይህም በጀት ለወሰን ማስከበር፣ ማማዎችን ለመገንባት፣ ጊዜያዊ ቢሮዎችን ለማቋቋምና ሌሎች ተያያዥ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚውል ጠቁመዋል።

የቀጣይ ምዕራፍ ግንባታም የቢዝነስ ጥናቱን ተከትሎ ተጨማሪ በጀት በመመደብ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በተለይም የሀዋሳ ደረቅ ወደብ ግንባታ ከአምስት ዓመታት በፊት የተጀመረ መሆኑን አንስተው፤ ከመሬት አቅርቦት ጋር ተያይዞ ለረዥም ጊዜ መጓተቱን አስረድተዋል።

ይህም ሆኖ አሁን ላይ እነዚህ ችግሮች እልባት አግኝተው የግንባታ ሥራ ለመጀመር የቢዝነስ ጥናቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በ3 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው ይኸው የሀዋሳ የደረቅ ወደብ በቀጣዩ በጀት ዓመት መጀመሪያ የግንባታ ሥራው ይጀመራል ብለዋል።

በሃያ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈውን የጅማ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ግንባታ ለመጀመር የመሬት አቅርቦት በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የግንባታ ዲዛይኑ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ግንባታው እንደሚጀመር ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በስምንት የደረቅ ወደቦች ላይ በደንበኞች ፍላጎትና የሎጂስቲክስ አገልግሎቱን ለማሳለጥ በሚያስችል መልኩ የማስፋፊያ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተቋሙ የሚያከናውናቸው የአዳዲስ ደረቅ ወደብ ግንባታዎችና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳለጥ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም