አገልግሎቱ ለተጠቃሚዎች በድምፅ፣ በምስልና በሌሎችም አማራጮች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ አደረገ

281

 

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ለተጠቃሚዎች በድምፅ፣ በምስልና በሌሎችም አማራጮች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ አደረገ።

የተቀናጀ የቤተ-መጻሐፍት የቤተ-መዛግብትና ሪከርድ ማኔጅመንት (ኢላርም) መተግበሪያ በ31 ሚሊዮን ብር ወጪ በአንድ ዓመት የተከናወነ ፕሮጀክት መሆኑም ታውቋል። 

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ዳይሬክተር ይኩኖ አምላክ መዝገቡ መተግበሪያው (ሶፍትዌሩ) ለፈጣን አገልግሎት ተደራሽነት የላቀ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

የበርካታ መጻሕፍቶችና ሰነዶች ሃብት ባለው ቤተ መጽሃፍት ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን መጻሕፍት፣ በድምፅ፣ በምስልና ሌሎችንም አማራጮች በመተግበሪያው የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

የአገልግሎቱ የኢንፎርሚሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ኤልሳቤጥ አሸናፊ፤ የመተግበሪያው እውን መሆን የሪከርድና ማኅደር ክፍል በደንብ ተደራጅቶ አገልግሎት እንዲሰጥም ያግዛል ብለዋል። 

በዚህም የቤተ-መጻሕፍቱን ካታሎጎች ማንኛውም ሰው ባለበት ስፍራ ሆኖ በሚጠቀምበት ዌብሳይት ፖርታል በመግባት ማግኘት እንደሚችል ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት በ1936 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለቤተመጻሕፍቱ ባበረከቱት መጻሕፍት ሥራ መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም