በሲዳማ ክልል በአምስተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ94 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል

269

ሀዋሳ፣ ግንቦት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል በአምስተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ከ94 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

የችግኞቹን መጠነ ጽድቀት ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችም ከወዲሁ እየተሰሩ እንደሆነ ተጠቁሟል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ፍቅረኢየሱስ አሸናፊ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ በዘንድሮ መርሃ ግብር 316 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።

ከሚያዚያ ወር ወዲህ አርሶ አደሮችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በተካሄደ ንቅናቄ የእቅዱን 30 በመቶ መፈጸም መቻሉን ገልጸዋል።

አብዛኛዎቹ የተተከሉት ችግኞች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመቋቋም አስተዋጽኦ ያላቸው እንደሆነ ጠቅሰው፤ እንደ ዋንዛ፣ ግራር፣ ጽድ፣ ቢርቢራ የመሳሰሉ ሀገር በቀል እና ለአርሶ አደሩ በቋሚነት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የቡናና የፍራፍሬ  ችግኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ለችግኝ ተከላ የሚሆኑ ከ200 በላይ ተራራዎች፣ የተራቆቱ አካባቢዎችና ሌሎችም መትከያ ስፍራዎች ተለይተው ከክልል ጀምሮ ባሉ ሁሉም መዋቅሮች ንቅናቄ በመፍጠር ዕቅዱን ለማሳካት እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

ለተተከሉት ችግኞች እንክብካቤ በማድረግ እንዲጸድቁ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለፃ፤ በክልሉ ባለፉት አራት ዓመታት አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ850 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መትከል ተችሏል።

ይህም ለአፈርና ውሃ እቀባ እንዲሁም የመሬትን ለምነትና እርጥበትን በማሻሻል ለምርትና ምርታማነት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

ከተተከሉት ፍራፍሬዎች መካከል የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎች ምርት በመስጠት ለይርጋለም የተቀናጀ ግብርና ፓርክ ግብዓት ሆኖ እየቀረበ እንደሆነም ተናግረዋል።

የዳራ ሆጢልቾ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መንግስቱ ማቲዎስ በበኩላቸው ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ስኬታማነት በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ወረዳው ዘንድሮ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ማቀዱን ጠቅሰው፤ እስካሁን  2 ነጥብ 5 ሚሊዮን  ችግኝ መትከል መቻሉን አመልክተዋል።

ቀሪውን ችግኝ ለመትከል በህብረተሰብ ተሳትፎ የችግኝ ጉድጓድ ቁፋሮ በዘመቻ እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በችግኝ ተከላ ተራቁቶ የነበረ ከ736 ሄክታር በላይ መሬት መልሶ በማገገም ወደ ልማት መግባቱን ጠቅሰው፤ በወረዳው የችግኝ መጠነ ጽድቀት 92 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለመሬት እርጥበትና ለምነት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ያሉት  ደግሞ የብላቴ ዙሪያ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ላሚሶ ዴራሞ ናቸው።

ልማትን በተቀናጀ መንገድ መምራት የሚያስችል ንቅናቄ ተፈጥሮ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘንድሮ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በወረዳው ይተከላል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም