አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ እና በኩዌት መካከል የሰራተኛ ስምሪት ስምምነት እንዲፈረም ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ እና በኩዌት መካከል የሰራተኛ ስምሪት ስምምነት እንዲፈረም ጠየቁ
አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ እና በኩዌት መካከል የሰራተኛ ስምሪት ስምምነት በአጭር ጊዜ እንዲፈረም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጠየቁ
ሚኒስትር ዴኤታው ዛሬ በኢትዮጵያ የኩዌት አምባሳደር ናይፍ ሃኘስ አል ኦይታይቢን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ እና በኩዌት መካከል የሰራተኛ ስምሪት ስምምነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈረም የሚደረገው ዝግጅት እንዲፋጠን ጠይቀዋል።
የሁለቱ አገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በሚጀመርበት ሁኔታ ዙሪያም ውይይት ያደረጉ ሲሆን ከወዲሁም አስፈላጊ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እና ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረት የኩዌት መንግስት እንዲደግፍም አምባሳደር ምስጋኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የኩዌት አምባሳደር ናይፍ ሃኘስ አል ኦይታይቢ በበኩላቸው በሁለቱ ሃገራት መካከል የሰራተኛ ስምሪት ስምምነት በአጭር ጊዜ እንዲፈረም የኩዌት መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እና የኩዌት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባው እንዲጀመር አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።