የኢዜአ አመራርና ሠራተኞች ለ12ኛ ጊዜ ደም ለገሱ

153

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ አመራርና ሠራተኞች ለ12ኛ ጊዜ ደም ለገሱ።

"በደም እጦት ሰው መሞት የለበትም" የሚለውን የዓለም ጤና ድርጅት መርህ ተግባራዊ ለማድረግ በተለያዩ አገሮች ዜጎቻቸው ደም መለገስን ባህል አድርገው ቀጥለዋል። 

በዚህ ተግባር አንዳንድ አገሮች ስኬታማ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ የድርጅቱን መርህ ለመተግበር በጥረት ላይ ይገኛሉ።

በአንድ አገር ሰው በደም እጦት እንዳይሞት ከአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር 1 በመቶ ደም መስጠት እንዳለበት ይታመናል።

በኢትዮጵያ በደም እጦት ሰዎች እንዳይሞቱ ለማስቻል በየሦስት ወሩ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች ደም መለገስ ይጠበቅባቸዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት ግን የደም ለጋሾች ቁጥር ከግማሽ ሚሊየን ያነሰ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በተለያዩ ጊዜያት የደም ልገሳ በማድረግ የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ይገኛሉ።

በመሆኑም የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች በዛሬው እለት ለ12ኛ ጊዜ የደም ልገሳ መርሃ-ግብር አካሂደዋል።
 

ከደም ለጋሾቹ መካከል ጋዜጠኛ በሀብቱ ተሰማ በተደጋጋሚ ልገሳ ያደረገ ሲሆን፤ የእናቶችና ህፃናትን ሕይወት ለመታደግ አስተዋጽዖ በማድረጌ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል ብሏል።

የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ሁሉም የደም ልገሳን ባህል በማድረግ ለሰብአዊነት እንዲተጋ መልዕክቱን አስተላልፏል።
 

ሌላው ደም ለጋሽ ጋዜጠኛ ሚኪያስ ጎቡ፤ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚደርሱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚሰጠውን ምላሽ የሚያግዝ መሆኑን ገልጿል።

ደም በመለገሱ መደሰቱንም ገልፆ፤ ማንኛውም ጤነኛ ሰው በየሦስት ወሩ ደም በመለገስ በደም እጦት ሕይወታቸው የሚያልፍ ወገኖችን  መታደግ አለበት ብሏል።


 

ሌላኛዋ የተቋሙ ሠራተኛ የንጉስ ውቤ፤ እስካሁን በተደረጉት የደም ልገሳ መርሃ-ግብሮች መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ በዛሬው እለትም ደም በመለገሳቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
 

በኢዜአ የሴቶች እና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክተርና የፕሮግራሙ አስተባባሪ ታደለች ቦጋለ፤ የተቋሙ ሰራተኞች በየሶሰት ወሩ ደም መስጠትን ባህል አድርገው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በተለያዩ ምክንያቶች ደም የሚሹ ወገኖች ሁላችንም ደማችንን በመለገስ ህይወታቸውን ማትረፍ አለብን ብለዋል።

የተቋሙ ሰራተኞች በተከታታይ የደም ልገሳ መርሃ ግብር በማከናወን ባህል አድርገው የቀጠሉ ሲሆን በዛሬው እለትም ለ12ኛ ጊዜ ደማቸውን ለግሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም