አገር አቀፍ የሥነ-ምግባርና የሙስና መከላከል ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል - የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
አገር አቀፍ የሥነ-ምግባርና የሙስና መከላከል ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል - የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን
አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015(ኢዜአ)፦ አገር አቀፍ የሥነ-ምግባርና የሙስና መከላከል ረቂቅፖሊሲ መዘጋጀቱን የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው ገለጹ።
ኮሚሽኑ ፖሊሲውን በሚመለከትና አሰራሩን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ እየሰራ ያለውን ሥራ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ሙስና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አንስተዋል።
የሙስና ወንጀል በዜጎች የዕለት ዕለት እንቅስቃሴ ላይ እያደረሰ ያለው አሉታዊ ጫና ማኅበራዊ ቀውስ እያስከተለ ከመሆኑ ባሻገር አገራዊ ሥጋት ሆኗል ነው ያሉት።
በመሆኑም በአገር አቀፍ ደረጃ የጸረ ሙስና ትግሉን ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችል አገር አቀፍ የሥነ-ምግባርና የሙስና መከላከል ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
ረቂቅ ፖሊሲው በጥናት ላይ የተመሰረተና የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ከግምት ያስገባ እንዲሁም የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ረቂቅ ፖሊሲ ነው ብለዋል።
ፖሊሲውን በሚመለከት የክልልና የከተማ መስተዳደር ተጠሪ ተቋማት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
ከዚህ ጎን ለጎን በውይይቱ በሙስና ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራትን በቴክኖሎጂ አሰራር ለመደገፍ የተከናወኑ ተግባራትም ውይይት እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም የሃብት ምዝገባን ጨምሮ የሙስና ወንጀል ጥቆማ የሚከናወንበት ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅና በቀጣይ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር መዘጋጀቱንም አክለዋል።
ውይይቱ ዛሬን ጨመሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ይሆናል።