አገራት በሳይበር ምህዳሩ ዘላቂ የሆነ ጥቅም ለማግኘት ትውልድ ተሻጋሪ የአቅም ግንባታ ስራ መስራት ይገባቸዋል - አቶ ሰለሞን ሶካ

353

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015(ኢዜአ)፦ አገራት በሳይበር ምህዳሩ ዘላቂ የሆነ ጥቅም ለማግኘት ትውልድ ተሻጋሪ የአቅም ግንባታ ስራ መስራት እንደሚገባቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።

በሞሮኮ እየተካሄደ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ (ጂአይቴክስ) ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን "የሳይበር ደህንነት አቅም ግንባታ ስራ ለሙያዊ ልህቀትና ለኢኮኖሚ ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት ተደርጓል።

በአውደ ርዕዩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ በትውልድ መካከል የሚፈጠሩ የእውቀት ክፍተቶችን ለመሙላት ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

እንደ ኢመደአ ያሉ የሳይበር ምህዳር ላይ የተሰማሩ ተቋማት የሰው ኃይል አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ድጋፍ መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢመደአ ብቁ እና ወሳኔ ሰጪ አመራር ለማፍራት የሚያስችሉ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

የሰው ኃይልን ከትምህርት የተመረቁ ብቻ ይዞ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ቀጣይነት ያለውን የበቃ የሰው ሃይል ልማት ማስቀጠል ስለማይቻል ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች መልምሎ እና እውቀታቸውን ለማጎልበት መስራት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

በተያያዘም የሳይበር ጥቃት ከዓለማችን ቀዳሚ ስጋቶች አንዱ መሆኑንና ምህዳሩ ፍጹም ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር አገራት በሳይበር ምህዳሩ ላይ በሚሰሩ ስራዎች ላይ በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩበት እንደሚገባ መግለጻቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ነገ ይጠናቀቃል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም