የታክስና የጉምሩክ ሕግ ተገዥነትን በማረጋገጥ ለአገር ዘላቂ ልማትና የሕዝብ ተጠቃሚነት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል - የገቢዎች ሚኒስቴር

169

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015 (ኢዜአ)፦ የታክስና የጉምሩክ ሕግ ተገዥነትን በማረጋገጥ ለአገር ዘላቂ ልማትና የሕዝብ ተጠቃሚነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የገቢዎች ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

የገቢዎች ሚኒስቴር ከየካቲት እስከ የካቲት "ግብር ለአገር ክብር" በሚል መሪ ሃሳብ በታክስ እና የጉምሩክ ሕግ ተገዥነት ላይ ያተኮረ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ንቅናቄ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አዲሱ ይርጋ በታክስ ዙሪያ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ በአገር አቀፍ ደረጃ የንቅናቄ መርሃ-ግብር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዘርፉ ስኬት በተለይም የኅብረተሰቡ እገዛና ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሀገር ልማትና ለሕዝብ ተጠቃሚነት በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የታክስ ስወራና ማጭበርበርን በመከላከል የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማት መደገፍ የሁሉም ዜጋ አገራዊ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ።

የንቅናቄ መርሃ-ግብሩ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ የራሱን አስተዋጽዖ እያበረከተ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የኅብረተሰቡና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ይበልጥ በማጠናከር በዘርፉ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ይሰራል ብለዋል።

ከታክስ ጋር በተያያዘ አብዛኛው የሕግ ጥሰት የሚፈጸመው ሕግን ባለማወቅና ከግንዛቤ እጥረት መሆኑን ጠቅሰው በወንጀሉ የሚሳተፉ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ቅንጅታዊ ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ፤ ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረትና በታክስ ላይ የሚፈጸመውን ማጭበርበር ለመከላከል የቀረበውን አዋጅ ማጽደቁ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም