በጅማና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ቅድመ ዝግጀት ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በጅማና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ቅድመ ዝግጀት ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለጸ
ጅማ/ነቀምት ግንቦት 24/2015:-በጅማና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ቅድመ ዝግጀት እየተጠናቀቀ መሆኑን የየዞኖቹ ግብርና ጽህፈት ቤቶች ገለጹ።
በጅማ ዞን ብቻ ለ5ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞች የሚተከሉ መሆኑ ተገለጿል።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድ ጣሃ አባፊጣ እንደተናገሩት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በዘመቻ እንዲሁም በተቋማት አማካይነት የሚከወን መሆኑንና የመትከያ ቦታዎች እየተዘጋጁ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከዚህ ቀደም በዞኑ ያልተለመዱ እንደ ቀርቃሃ እና ቴምር ያሉ ችግኞችም የሚተከሉ ይሆናል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የተተከሉ ችግኞችን ከመንከባከብ አንጻር የጽድቀት መጠኑ 80 በመቶ ሲሆን ይህም የሚበረታታ መሆኑን ነው ሀላፊው የተናገሩት።
በዞኑ የነዲ ጊቤ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ነዚፋ አወል፣ በዚህኛው ዙር 100 ችግኝ ለመትከል ቦታ ያዘጋጁ መሆኑን እና በዘመቻ የሚተከለውንም ለመሳተፍ ተዘጋጅተዋል።
ሌላው የዴዶ ወረዳ አርሶ አደር ወጣት ናስር አባ ጀበል በበኩሉ በየአመቱ የተለያዩ ችግኞችን በማሳው ዳርቻ እንደሚተክል ገልጾ ዘንድሮም 50 የተመረጡ የዛፍ ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀቱን ተናግሯል።
''ከዚህ በፊት የተከልኳቸውን ችግኞች በመንከባከብ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰዋል'' ያለው ወጣቱ ''አሁንም እንደ ዋንዛ እና ግራር የመሳሰሉ ዞፎችን እተክላለሁ'' ብሏል።
በተመሳሳይ በምሰራቅ ወለጋ ዞን በመጪው ክረምት 400 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡
በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ስራ ሂደት ሃላፊ አቶ ደሳለኝ በለታ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የችግኝ እና ጉድጓድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
እሰካሁን በተሰራ ስራ በ2 ሺህ 148 ችግኝ ጣቢያዎች 378 ሚልዮን ችግኝ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
እየተዘጋጁ ከሚገኙት ችግኞች መካከል ለእንስሳት መኖ፣ ቀርከሃ፣ ፍራፍሬ እና የተለያዩ ዛፎች ይገኙበታል ብለዋል፡፡
በዞኑ ለዚሁ አላማ የሚውል 39 ሺህ ሔክታር መሬት ተዘጋጀ ሲሆን 182 ሚልዮን የችግኝ መትከያ ጉድጓድ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።