ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 

302

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015 (ኢዜአ):-  ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ጋር በመተባበር ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሥልጠና እየሰጠ ነው። 

ሥልጠናው መገናኛ ብዙኃን ጸጥታና ደኅንነት በማረጋገጥ እንዲሁም ድንበር ዘለል የጸጥታ ሥጋት በመከላከል ሚናቸውን ማጎልበት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ትኩረት አድርጓል ተብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሚደረገው እንቅስቃሴ ዲፕሎማቶች ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኞችም ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

በመሆኑም ጋዜጠኞች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ገልጸው በተለይም ደግሞ ትክክለኛ መረጃዎችን በማሰናዳት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።


 

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ጀማላዲን መሃመድ በበኩላቸው ሥልጠናው ጋዜጠኞች በጸጥታ ጉዳዮች ያላቸውን ግንዛቤ ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።   

በተለይም በግጭትና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት በተሞላበት አኳኋን እንዲሰሩ እንዲሁም ትክክለኛና ሚዛናዊ ዘገባዎችን ለማቅረብ አስፈላጊውን እውቀትና ክህሎት ለማዳበር የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የኢጋድ አባል አገራት ድንበር ተሻጋሪ የጸጥታ ሥጋቶችን ለመቅረፍ የአባላትን አቅም ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ጋዜጠኞች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንደሚረዳ ገልጸዋል። 

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የጸጥታና ደኅንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በበርካታ ድንበር ዘለል የጸጥታና ደኅንነት ሥጋቶች ያሉበት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም መገናኛ ብዙኃን በቀጠናው የሚያጋጥሙ የጸጥታ፣ ደኅንነትና ወንጀል ሥጋት በአግባቡና በትክክለኛው መንገድ በመገንዘብ  ገጽታ የሚገነቡና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩ ሥራዎችን በትኩረት መሥራት አለባቸው ነው ያሉት። 

በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንት ማረጋገጥ ብዙኃኑን ያሳተፈ ሁለገብ ሥራን የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙኃን የድርሻቸውን ጉልህ ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቁሟል። 

የመገናኛ ብዙኃን ግጭትን መከላከል ብቻ ሳይሆን በድህረ ግጭት የሰላም ግንባታ እንዲሁም ደግሞ ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት። 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም