ህብረተሰቡ ደህንነቱ የተረጋገጠ ምግብና መድኃኒቶችን ለይቶ እንዲጠቀም መገናኛ ብዙሃን በማስገንዘብ እንዲያግዙ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ ደህንነቱ የተረጋገጠ ምግብና መድኃኒቶችን ለይቶ እንዲጠቀም መገናኛ ብዙሃን በማስገንዘብ እንዲያግዙ ተጠየቀ

ባህርዳር ግንቦት 24 / 2015 (ኢዜአ) ፡- ህብረተሰቡ ደህንነቱና ጤንነቱ የተረጋገጠ ምግብና መድኃኒትን በመለየት እንዲጠቀም ተከታታይ ግንዛቤ በመፍጠር የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንዲያግዙ ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአማራ ክልል ከሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ለተወጣጡ ባለሙያዎች ህገ ወጥ ምግብና መድኃኒት በሚያደርሱት ጉዳት መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ዙሪያ በደብረታቦር ከተማ ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄዷል።
በባለስልጣኑ የቅርንጫፎች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገዛኽኝ እንዳለ በወቅቱ እንዳሉት፤ መስሪያ ቤቱ የህብረተሰቡን የጤና ደህንነት ለመጠበቅ የቁጥጥርና የክትትል ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በህገ ወጥ መንገድ ከውጭ የሚገቡና በሀገር ውስጥ የሚመረቱ፣ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውና የትና በማን እንደተመረቱ የማይታወቁ ምግብና መድሃኒቶች በህዝቡ ጤና ላይ እክል እየፈጠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
እነዚህ ህገወጥ ምግቦችና መድኃኒቶችም ለደም ግፊት፣ ካንሰር፣ ስኳርና ሌሎች የጤና ጉዳቶች እንደሚያጋልጡ ተናግረዋል።
ችግሩን በማቃለል የህብረተሰቡን ጤንነት ተጠብቆ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠርም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተከታታይ ትምህርት በመስጠት እንዲያግዙ ጠየቀዋል።
በባለስልጣኑ የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የምግብ ተቆጣጣሪ አቶ መለሰ እንግዳየሁ በበኩላቸው፤ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የህፃናት ወተት፣ ሴሪፋምና ሌሎች ምግቦች በስፋት በገበያው ላይ እንደሚስተዋሉ አስረድተዋል።
መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ህገ ወጥ ምግብና መድሃኒቶች እንዲወገዱ ከማድረግ ባለፈ በአጥፊዎች ላይ ፈቃድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።
ዘንድሮ በተደረገ ቁጥጥርም የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የለውዝ፣ የህፃናት ምግቦች፣ የተበላሸ የዳቦ ዱቄት፣ ሲጋራና የውሃ ማከሚያ ኬሚካሎች በመያዝ የማስወገድ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
የተወገዱት ምግብና ምግብ ነክ ዓይነቶችም መርዛማ በመሆናቸው ለኩላሊት፣ ለጉበት፣ ለሳንባና ለልብ በሽታ ህብረተሰቡን በማጋለጥ ለሞት የሚዳረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ይሄን የሚፈጽሙ ስግብግብ ነጋዴዎች የጋረጡትን አደጋ በማስገንዘብ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ ባለመሆኑ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች በትኩረት እንዲሰሩ አመልክተዋል።
"ህገወጥ ምግቦችና መድኃኒቶች በዜጎች ህይወት ላይ የከፋ አደጋን እንደደቀኑ ተገንዝቤአለሁ" ያለው ደግሞ የደብረብርሃን ፋና ኤፍኤም ዘጋቢ አበበ የሸዋልዑል ነው።
ህገ ወጥ ምግብና መድሃኒት እያደረሰ ያለውን ችግር ለህብረተሰቡ በማስገንዘብ የራሱን ጤና ከሚጎዱ ነገሮች ራሱን እንዲጠብቅ ሙያዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጿል።
በዚህም ወደ አካባቢው ሲመለስ በሚሰራቸው ዜናዎች ፕሮግራሞችና ሌሎች ዘገባዎችን በህገ ወጥ መድሃኒትና ምግብ አስከፊነትና መከላከያ መንገዱ በማተኮር ህዝቡን ለማስተማር እንደሚጥር ተናግሯል።
የአሚኮ ባልደረባ ጋዜጠኛ ታርቆ ክንዴ በበኩሉ፤ ህገወጥ ምግቦችና መድኃኒቶች ምን ያህል አስጊ እንደሆኑ ከመድረኩ በቂ እውቀትና ግንዛቤ ማግኘቱን ተናግሯል።
ህብረተሰቡ የሚጠቀማቸውን ምግቦችና የሚወስዳቸውን መድኃኒቶች የመጠቀሚያ ጊዜ ያላለፈባቸው መሆናቸውን አረጋግጦ እንዲወስድ የማስገንዘብ ስራው የዕለት ከዕለት ተግባሩ እንደሚሆን ገልጿል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ለሁለት ተከታታይ ቀናት መካሄዱ ታውቋል።