ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሌሎች የአፍሪካ አገራት አርአያ የሚሆን ነው - ኢሲኤ 

251

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የቴክኖሎጂ፣ የአየር ንብረት ለውጥና የተፈጥሮ ሃብት ዳይሬክተር ዦን ፖል አደም ተናገሩ። 

ዳይሬክተሩ ዦን ፖል አደም ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የምታካሂደው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የብዝሃ ሕይወት ጥበቃን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

ያም ብቻ ሳይሆን በመርሃ ግብሩ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት ማቀፉንም ነው የጠቆሙት።

ለአብነትም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ቡናን ማልማትና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊ አንድምታ ያላቸው እንቅስቃሴዎች እንዳሉት ተናግረዋል። 

ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ በተፋሰስ አካባቢ ብዝሃ ሕይወት በመንከባከብ የውሃ ሃብትን ለመንከባከብ  እየሰራች ያለው ሥራ የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል።  

በመሆኑም ይህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው የአረንጓዴ አሻራ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት በአርአያነት የሚጠቀስ መርኃ ግብር መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። 

ተቋማቸውም ይህንን የኢትዮጵያ ጥረት ስኬታማ ለማድረግ የሙያ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚያዊ ለውጥን እውን ለማድረግ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ዋነኛው መሆኑን ገልጸው በዘርፉ ሕዝቡን በበቂ ሁኔታ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የአፍሪካ አገራት ለዘርፉ አስፈላጊውን ትኩረትና በመስጠትና ከዘርፉ የሚያገኙትን ጥቅም ከፍ በማድረግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።  

የአፍሪካ አገራት በግብርናው ዘርፍ ዘላቂነት ያለው የእሴት ሰንሰለት በመፍጠር በቱሪዝም ዘርፍ ገቢን ማሳደግ እንደሚገባ ዳይሬክተር ዦን ፖል አደም ተናግረዋል።      

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም