'ጂ አይ ቴክስ አፍሪካ' በሞሮኮ ማራካሽ ከተማ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015 (ኢዜአ):- 'ጂ አይ ቴክስ አፍሪካ' 2023 /GITEX Africa 2023/ በሞሮኮ ማራካሽ ከተማ መካሔድ ጀምሯል።

በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው 'ጂ አይ ቴክስ አፍሪካ' ላይ ኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶክተር) በሚመሩትና የሚኒስቴሩ የስራ ኃላፊዎችና በውድድር የተመረጡ የቴክኖሎጂ ጀማሪ ካምፓኒዎች (ስታርታፖች) በተካተቱበት የልዑካን ቡድን እየተሳተፈች ትገኛለች።

በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከናወነ የሚገኘው 'ጂ አይ ቴክስ አፍሪካ' ተቀዳሚ ዓላማ በአህጉሯ እየተካሄደ የሚገኘውን የቴክኖሎጂ አብዮት ለተቀረው ዓለም ማስተዋወቅ ነው።

ባለፋት ሁለት አመታት መሠረታቸውን አፍሪካ ያደረጉ በርካታ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጣሪ ካምፓኒዎች በዓለምአቀፉ መድረክ በስፋት መታየት እና ተጽዕኖ መፍጠር ጀምረዋል።

ዶክተር በለጠ ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞን እውን ለማድረግ ባለፉት ሶስት ዓመታት ያከናወነቻቸውን ተግባራት፣ እያደረገች ያለውን ጥረቶች፣ የተገኙ ውጤቶችን እና ያጋጠሙ ችግሮችን ማብራሪያ መስጠታቸውን ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሚኒስትሩ በቀጣይ እንደ አፍሪካ በቅንጅት መካሄድ አለባቸው ባሏቸው ጉዳዮች ላይም ሃሳባቸውን ለመድረኩ አጋርተዋል።

አክለውም ኢትዮጵያ በርካታ ለስራ ዝግጁ የሆኑ ወጣቶች፣ ቴክኖሎጂን ትኩረት ያደረጉ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የዲጂታል ዘርፍ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ የህግ ማዕቀፍና ለስራ ዝግጁ የሆነ የአይ ሲቲ ፓርክ እንዳላትም አሳውቀዋል።

ሚኒስትሩ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ተጠቃሚ እንዲሆኑና እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል ።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም