የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2015 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለት ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።
በመርሃ ግብሩ ሲዳማ ቡና ከአርባ ምንጭ ከተማ ከቀኑ 7 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።
በደረጃ ሰንጠረዡ ሲዳማ ቡና በ34 ነጥብ 10ኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን አርባ ምንጭ ከተማ በ29 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ሲዳማ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ በአንዱ አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው አርባ ምንጭ ከተማ በአንጻሩ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በአራቱ ነጥብ ተጋርቷል።
ጨዋታው ሲዳማ ቡና ከወራጅ ቀጠና ስጋት ለመራቅ እንዲሁም አርባ ምንጭ ከተማ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚያደርጉት ጨዋታ መሆኑ ተጠባቂ ያደርገዋል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ ሶስት እኩል በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።
በሌላኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መርሐ -ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከለገጣፎ ለገዳዲ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በደረጃ ሰንጠረዡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ55 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ የተቀመጠ ሲሆን ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ለገጣፎ ለገዳዲ በ15 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሶስቱ አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው ለገጣፎ ለገዳዲ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን በሶስቱ ተሸንፏል በአንዱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ካሸነፈ ከተከታዩ ባህር ዳር ከተማ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ስምንት ከፍ ያደርጋል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 4 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እስከ ግንቦት 27/ 2015 ይቆያል።
የፕሪሚየር ሊጉ የውድድር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ በሃዋሳ ከተማ አመሻሽ ላይ በሚጥለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የሰዓት ማስተካከያ በማድረግ በ9 ሰዓት እንዲጀምሩ ፕሮግራም የወጣላቸው ጨዋታዎች በሙሉ 7 ሰዓት እንዲሁም በ12 ሰዓት ይጀምሩ የነበሩ ጨዋታዎች ደግሞ 10 ሰዓት ላይ እንዲጀመሩ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።
በተጨማሪም ተጀምሮ በዝናብ ምክንያት የተቋረጠ ጨዋታ ካለ በማግስቱ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ በሃዋሳ አርተፊሻል ሜዳ ላይ እንደሚጠናቀቅም ገልጿል።