አገራዊ ምክክሩ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት መደላድል የሚፈጥር ነው - የድሬዳዋ ሕብረተሰብ ተወካዮች  

ድሬዳዋ ግንቦት 23/2015 (ኢዜአ):- አገራዊ የምክክር መድረኩ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠርና አንድነትን በማጠናከር  የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት መደላድል እንደሚፈጥር የድሬዳዋ ሕብረተሰብ ተወካዮች ገለጹ። 

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን  በአገራዊ የምክክር ሂደት ላይ አጀንዳ ለማሰባሰብ ስለሚከናወኑ ተግባራትና  የውይይት ተሳታፊዎች ልየታን  አስመልክቶ በድሬዳዋ ለሁለት ቀናት ያዘጋጀው ስልጠና  ተጠናቋል ።

በስልጠናው ላይ  የተሳተፉ የድሬዳዋ ሕብረተሰብ ተወካዮች  እንዳሉት  በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የምክክር መድረክ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጥር  ወሳኝ የሽግግር ምዕራፍ  ነው።

ከድሬዳዋ መምህራን ማህበር የመጡት መምህርት ሙሉካ ሁሴን ስልጠናው በቀጣይ በሚካሄደው አገራዊ  ምክክር ተሳታፊዎችን የመለየት ሂደት ተአማኒነትና አሳታፊነትን ያሟላ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

“በአገር ደረጃ የሚካሄደው የምክክር መድረክ በዜጎች መካከል መቀራረብ እና አንድነትን በማጠናከር  የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ከፍታ ለማረጋገጥ ያስችላል” ብለዋል።

አገራዊ የምክክር መድረክ  አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ወሳኝ  መሆኑን  የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዮናስ በትሩ ናቸው።

በሰከነ መንፈስ መወያየት ለአገር ዘላቂ ሰላምና እድገት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንና የጋራ ምክር ቤቱ በቀጣይ የሚካሄዱ የምክክር ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል።

የድሬዳዋ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ጥምረት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አንድነት ዘነበ "ኢትዮያዊያን የሚያካሂዱት ምክክር አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር  መሰረት የሚጥል  ነው" ብለዋል።

የምክክር መድረኩ  ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አጀንዳዎች ላይ መግባባት የሚፈጥሩበት ብቻ ሳይሆን አንድነትና አቅም መፍጠር የሚያስችላቸው መሆኑን አመልክተዋል። 


 

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር እንዳሉት ኮሚሽኑ በሚያከናውነው  የተሳታፊዎች ልየታ የተለያዩ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት የሂደቱን ግልጸኝነት ፣አሳታፊነትና ተአማኒነት የመታዘብና የማረጋገጥ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

የምክክር  መድረኩ  ኢትዮጵያውያንና  ትውልደ ኢትዮጵያውያን  ጨምሮ ሁሉንም የሚያሳትፍ  በመሆኑ  ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ  ምዕራፍ ለማሻገር መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

በሰከነ መንገድ በመወያየት የጋራ አገራዊ መግባባት በመፍጠር ኢትዮጵያን ለማሻገር እንደሚያስችል አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም