ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እየሰሩ እንደሚገኙ የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ

ደብረ ብርሃን ግንቦት  23 / 2015  (ኢዜአ):- አብሮነትን በማጠናከር የአካባቢያቸውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች አስታወቁ። 

በአማራ ክልል የአንጎላላ ጠራ ወረዳ  እና በኦሮሚያ ክልል  የቅንቢቢት ወረዳ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላምን ማስፈንና ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የጋራ ውይይት ዛሬ አካሄደዋል።

ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጎላላ ጠራ ወረዳ ተሳታፊ  የሆኑት መላከ መዊዕ ቀሲስ ገዛኸኝ ኃይሉ እንደገለጹት፤ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ በአንድነት፣ በፍቅር እና በመተሳሰብ የሚኖር ነው።

ለሕዝቡ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትንና መተሳሰብን መሰረት አድርገው በማስተማር የአካባቢያቸው ሰላም በዘላቂነት እንዲጠበቅ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቅንቢቢት ወረዳ የመጡት ቄስ ተሰማ በላቸው በበኩላቸው በሕዝቦች መካከል ፍቅርና ሰላም ጸንቶ እንዲዘልቅ ወጣቶችን እያስተማርን ነው ብለዋል።

የሕዝቦች አብሮ የመኖር እሴት እንዲጎለብትና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማስተማር የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከቅንቢቢት ወረዳ የመጡት የአገር ሽማግሌ አቶ ተስፋዬ ግርማ በበኩላቸው በአካባቢው የሚኖሩ የኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦች ከትውልድ ትውልድ የተሻገረ የጋራ ታሪክና እሴት እንዳላቸው አውስተዋል።

"የብሔር ልዩነት ሳይገድበን አብረን የምንኖር ሕዝቦች በመሆናችን የጀመርነውን የጋራ እድገት፣ ልማትና ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ጥረት አጠናከክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት የአገር ሽማግሌ አቶ ተስፋዬ ሞገስ በበኩላቸው  ከኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ወረዳ ሕዝቦች ጋር በፍቅርና በሰላም የምንኖረው በመማከርና በመወያየት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አለመግባባቶች ሲኖሩ  የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ጋር በመመካከር እየፈቱ እንደሚገኝና በዚህም የአካባቢው ሰላም ተጠብቆ መቆየቱን ተናግረዋል።

"የአካባቢያችንን ሰላም ለማደፍረስ  የሚጥሩ ኃይሎችን እኩይ ሴራ ቀድሞ በማክሸፍ ሰላሙ ጽንቶ እንዲዘልቅ በጋራ የጀመርነው ውይይትና ምክክር ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ከአካባቢያቸው ባለፈ በአገር አቀፍ ደረጃ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም