የሲዳማ ክልል የህዝብ አደረጃጀቶች የህዝብ ጥያቄዎች ለአገራዊ ምክክር መድረክ እንዲቀርቡ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገለጹ 

ሀዋሳ ግንቦት 23/2015 (ኢዜአ) የህዝብ ጥያቄዎች ለአገራዊ ምክክር መድረክ እንዲቀርቡ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በተባባሪነት የተለዩ የሲዳማ ክልል የህዝብ አደረጃጀቶች አስታወቁ።

ኮሚሽኑ በተሳታፊ ልየታና አጀንዳ መረጣ ላይ ለሚሳተፉ ተባባሪ አካላት በሀዋሳ ከተማ ባዘጋጀው ስልጠና ላይ የተሳተፉ የሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የእድርና ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የኮሚሽኑ ስራ በስኬት እንዲጠናቀቅ የዜጎች ያልተቆጠበ ተሳትፎ ያስፈልጋል።

በመሆኑም በምክክሩ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮችን የመምረጥ ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በሲዳማ ክልል ሴቶች ማህበር የሲቪክ ማህበረሰብ ተወካይ ወይዘሮ ዘውዲቱ ጥላሁን በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሚከናውነው ታላቅ ተልእኮ በተባባሪነት መመረጣቸው ከፍተኛ ሃላፊነት እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህን ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉ ሴቶች ድምጽ እንዲሰማ ለማድረግ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በሰላም ማጣት የበለጠ ተጎጂ ከሚሆኑት ማህበረሰብ ክፍሎች ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በሂደቱ ሴቶች በንቃት እንዲሳተፉ ለማስቻል እንሰራለን ብለዋል።

የመልጋ ወረዳ አካል ጉዳተኞች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ሃየሶ ሃሶ በበኩላቸው በብሄራዊ ምክክር ሂደቱ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንዲኖር መደረጉ በርካታ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል።


 

በስልጠና መድረኩ ያገኙትን ግንዛቤ ተጠቅመው በምክክር መድረኩ ተገቢውን ሃሳብ ሊያንሸራሽሩ የሚችሉ ተወካዮችን በመምረጥ ከብሄራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍታት የሀገርን ህልውና ለማስቀጠል የብሄራዊ ምክክሩ አስፈላጊነት በዜጎች ቅቡልነት ያገኘ ነው ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካይ አቶ ሃብተማርያም አብዩ ናቸው።

የማያስማሙን ጉዳዮች ቢኖሩ እንኳን በአገር ሰላምና አንድነት ላይ ባለመደራደር የንግግር ባህልን ማሳደግና ከችግሩ ለመውጣት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በሀዋሳ ከተማ የመሀል ክፍለ ከተማ እድር ተወካይ አቶ መስፍን ዘውዴ በበኩላቸው አገራዊ ምክክሩ ለግጭት መንስኤ እየሆኑ ላሉ በርካታ ችግሮች መፍትሄ የሚሰጥ በመሆኑ ብርቱ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

እድሮች የተለያየ ህብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍባቸው እንደመሆናቸው መጠን ለሀገር ጠቃሚ ሃሳቦችን ማመንጨት እንደሚችሉ አመልክተዋል።

በመሆኑም የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ አካላትን በመምረጥ የህዝቡን ችግር በተገቢው የሚያሳይ አጀንዳ ለመምረጥ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብና ምክክር ላይ የሚሳተፉ አባላትን ለሚመለምሉ ተባባሪ አካላት በሀዋሳ ስልጠና መስጠቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም