'መለኞቹ' የተሰኘ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጀብድ ላይ ያተኮረ ፊልም ለዕይታ በቃ - ኢዜአ አማርኛ
'መለኞቹ' የተሰኘ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጀብድ ላይ ያተኮረ ፊልም ለዕይታ በቃ
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2015 (ኢዜአ) 'መለኞቹ' የተሰኘ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጀብድ ላይ ያተኮረ ፊልም ለዕይታ በቃ።
ፊልሙ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተመርቆ ለእይታ በቅቷል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ፣ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤልና ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ውጤታማ የሪፎርም ሥራዎች ከተተገበሩበት የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት መካከል የፌዴራል ፖሊስ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ፊልሙ የፌደራል ፖሊስ ህዝቡን በማገልገል ረገድ ያከናወነውን አኩሪ ታሪክ ለትውልድ ሰንዶ በማስተላለፍ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም መሰል ተግባራት በሌሎች ተቋማትም ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀደምት ከሆኑ የኢትዮጵያ ተቋማት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
በረጅም ጊዜ ተቋማዊ ታሪኩም ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካ ሰላም መሥራቱን ነው ያወሱት።
ለአብነትም በተባበሩት መንግሥታት ደርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም የፖሊስ ድርጅት (ኢንተር ፖል) ከምሥረታው ጀምሮ አባል መሆኗንም ነው ያነሱት።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረትን በፕሬዝዳንትነት በመምራት ላይ መሆኗን ጠቅሰው ለዚህም በተለይም በሪፎርሙ የተገኙ ስኬቶችን በማጋራት ለቀጣናው ሰላም እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
ፊልሙ በእውነተኛ ታሪክ ለይ የተመሰረተ ሲሆን የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጭምር በትወና መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።
የፌደራል ፖሊስ የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅ ሃላፊነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።