ብልፅግና ፓርቲ በሰጠው ጠንካራና ቅቡልነት ያለው አመራር የሀገረ መንግስት ግንባታን የሚያፋጥኑ ስራዎች ተከናውነዋል - የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ

215

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2015 (ኢዜአ)፦ብልፅግና ፓርቲ በሰጠው ጠንካራና ቅቡልነት ያለው አመራር የሀገረ መንግስት ግንባታን የሚያፋጥኑ ስራዎችን ማከናወን መቻሉን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳን አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

ፓርቲው የተጀመሩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች በስኬት እንዲቀጥሉ የፓርቲውን አመራር የማጥራት፣ የማጠናከርና የመገንባት ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ በቆየው መደበኛ ስብሰባ ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎችና ነገ የሚጀመረውን የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ በማስመልከት ለኢዜአ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በዲፕሎማሲያዊ ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶችን ገምግሞ የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል ብለዋል፡፡

በፖለቲካው ዘርፍ የጋራ መግባባት ያልተደረሰባቸው መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በምክክር ኮሚሽኑ አማካኝነት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው ጥረት መልካም መሆኑ ተገምግሟል ነው ያሉት፡፡

የብልጽግና ፓርቲም ሁሉንም አሳታፊ ውይይት እንዲደረግ እና የጋራ ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ እንደ አንድ ፓርቲ የበኩሉን ሚና እንዲያበረክት አቅጣጫ መቀመጡን አንስተዋል፡፡

ፓርቲው በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓትን ለማንበር በርዕዮትና በፖሊሲ የሚለዩትን የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግስት መዋቅር ውስጥ በማሳተፍ የትብብር መንፈስ እንዲፈጠር አድርጓል፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂና አወንታዊ ሰላም ለመፍጠር ለህዝብ ጥቅም የቆሙ ነፃና ገለልተኛ የጸጥታና ደህንነት እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ ከነበሩ አካላት ጋር ዘመናዊና ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ያጣመረ ውይይት በማካሄድ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጥረት መደረጉ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በአዎንታዊነት እንደተገመገመ ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቡድንና የግል ፍላጎትን በኃይል ለማሳካት ያሰቡ ጽንፈኛ አካላት ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን እየፈተኑት ነው ያሉት አቶ አደም፤ ነፃነትን ለመጠቀም የሌሎችን ነፃነት ማክበር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የህግ የበላይነትንና ህገ መንግስታዊነትን ማረጋገጥ፣ የተሟላ ሀገራዊ ሰላምን ማፅናት፣ የፍትሕና ፀጥታ ተቋማትን ማጠናከር፣ የሁለም ኢትዮጵያውያን የወል እውነቶችን ገዥ ቦታ እንዲይዙ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል።

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ባለፉት 10 ወራት ፍትሐዊ ልማትን ከማረጋገጥ አንጻር አካታች ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን በውይይቱ እንደተመለከተም አብራርተዋል።

የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ስርዓትን በማስቀጠል የተመዘገቡ ስኬቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ በተለይም በስንዴ ምርታማነት የታየውን ውጤት በትልቅ ስኬት ማነሳቱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ችግር በመፍታት፣ ምርታማነትን ለማሳደግና የገበያ ትስስር በመፍጠር አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በገበታ ለሀገር እና ሌሎች ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት መቻሉን እንዲሁም ከስራ ዕድል ፈጠራ አኳያ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የዋጋ ንረትን ለማረጋገት፣ ኮንትሮባንድን ለመከላከል፣ በአምራችና ሸማቹ መካከል እሴት የማይጨምሩ የገበያ ሰንሰለቶችን ለመቀነስ ጠንካራ ርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ አካታች የማህበራዊ ልማትን ለማጎልበት በትምህርት፣ በጤና እንዲሁም በወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት ላይ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በማህበራዊ መስክ ያሉ የትምህርት ጥራት፣ ፍትሐዊነትና እኩል ተጠቃሚነትን መሰረተ ያደረገ ሥነ ምግባራዊና ሀገር ውዳድ ትውልድ ግንባታ ይከናወናል ብለዋል፡፡

ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረጉ የዲፕሎማሲ ስራዎች ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው፤ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ በመስጠት የኢኮኖሚ ትስስር ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

የሀገርን ክብር የማስጠበቅ አካሄዳችን ያልተመቻቸው አካላት የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ የፈጠሩብንን ጫና በመቋቋም የሀገር ሉዓላዊነታችንና የግዛት አንድነታችንን አስጠብቀን ቀጥለናል ብለዋል፡፡

ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የመስጠት መርህ ውጤት በማስገኘቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ሚዛኑን የጠበቀ ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን በመከተል የፖሊሲ ነጻነታችንን የሚጋፉና ፍትሐዊ ተጠቃሚነታችንን እንዳናረጋገጥ የሚፈትኑ ጫናዎችን የመመከትና ወዳጅነትን የማስፋት ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ መቀመጡን አንስተዋል።

ብልጽግና ፓርቲ የተጀመሩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች በስኬት እንዲቀጥሉ የፓርቲውን አመራር የማጥራት፣ የማጠናከርና የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ፈጠራና ፍጥነትን ተጠቅሞ የፓርቲውን አደረጃጀት ማጠናከር፣ የውስጠ ፓርቲ አንድነትና ዴሞክራሲን ማጎልበት፣ ብሎም በምርጫ ወቅት ለህዝብ የተገባውን ቃል በውጤታማነት መፈጸም የቀጣይ ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም