ለዘላቂ ሰላም መስፈን የድርሻቸውን እንደሚወጡ የጌዴኦ ዞን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ

ዲላ  ግንቦት 23/2015 (ኢዜአ) ለዘላቂ ሰላም መስፈን የድርሻቸውን እንደሚወጡ የጌዴኦ ዞን የቤተ እምነት መሪዎችና የባህል አባቶች አስታወቁ።

የሰላም እሴቶችን ለማጽናትና ግጭቶችን አስቀድሞ መከላከልን ዓላማው ያደረገ የሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ የሚመክር መድረክ ዛሬ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ  የቤተ እምነት መሪዎች፣ የባህልና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የጌዴኦ ዞንና የዲላ ከተማ አስተዳደር  የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል  በኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን የልማት ካውንስል ዳይሬክተር መጋቢ ቦካኮ ዱጉማ እንዳሉት ስለ ሰላም መስራት የቤተ እምነቶች ተቀዳሚ ተልዕኮ ነው።

"ልጆቻችንን ስናሳደግ ጥላቻና በደል እያስተማርን  ሳይሆን ለሀገርና ለወገን የሚበጀውን ስለ ፍቅር፣ ሰላም፣ አብሮነትና አንድነትን በመመገብ ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

በተለይም ታሪክን ለአገር ግንባታና ለትውልድ ትምህርት መውሰድ እንጂ የጠብና የግጭት ምንጭ አድርገን መተረክ እንደማይገባ አስገንዝበዋል።

የቋንቋና የሃይማኖት ልዩነቶች ውበትና ጸጋዎች መሆናቸውን ተረድተን ከአክራሪነትና የኔ ብቻ ከሚል ጽንፈኝነት ይልቅ ለሰላምና ለመቻቻል ቅድሚያ መስጠት ይገባል ብለዋል።

በተለይም በሀገራችን የመጣውን የሰላም አየር ዘላቂና ወንድማማችነትን ያጎለበተ እንዲሆን ግንባር ቀደም ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

የጌዴኦ ብሔር ባህላዊ የባሌ አስተዳደር መሪ አባ ገዳ ቢፎሚ ዋቆ በበኩላቸው በሀገራችን የሚገኙ በርካታ ባህሎች ለሰላም ግንባታ ጠቃሚ እሴቶች ያሉ ቢሆንም በአግባቡ ከመጠቀም አንጸር ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የባህል አባቶችና የቤተ እምነት መሪዎች "ግጭትን ለማስቀረት የምናደርገውን ጥረት ያክል ያገኝነውን የሰላም አየር ዘላቂ ለማድረግም ልንሰራና ልንጥር ይገባል" ብለዋል።

በተለይም በውስጣችን ለግጭት መነሻ የሆኑ አስተሳሰቦችን በውይይት የመፍታት ባህላችንን በማሳደግ ለትውልዱም ሆነ ለሀገራችን የፖለቲካ ስርዓቱ ምሳሌ መሆን ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።

የሰላም እሴቶችን ማስተዋወቅና ማስተማር ለዘላቂ ሰላም መሰረት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጌዴኦ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ካውንስል ሰብሳቢ ቄስ አያሌው ሙርቲ ናቸው። 

የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ከጥላቻና መገፋፋት ይልቅ ወንድማማችነትንና ወዳጅነትን እንዲያስቀድሙ የጋራ እሴቶች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ምስጋና ዋቀዮ በበኩላቸው በሀገራችን የመጣውን የሰላም ሁኔታ ሊያሻክሩ የሚችሉ ጽንፈኝነትን በጋራ መከላከል ይገባል ብለዋል።

በተለይም በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ጥላቻና ግጭትን የሚሰብኩ የፖለቲካ ነጋዴዎች ተቀባይነት እንዳያገኙና ትውልዱን በሰላም እሴቶች በመገንባቱ ረገድ የቤተ እምነት መሪዎችና የባህል አባቶች ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአንጻሩ ወንድማማችነትን የሚያጎለብቱ መድረኮችን በማጠናከር ሀገራዊ ሰላማችንን ዘላቂ በማድረጉ ረገድ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተስፋጽዮን ዳካ በበኩላቸው በህብረተሰቡ ዘንድ መግባባት እና መተማመን በመፍጠር ፍፁም የሆነ ሰላም ማምጣት እንደሚቻል አመላክተዋል።

ከግጭት የሚያተርፉ አካላት መቼውንም ጊዜ ለሰላም ፍላጎት የሌላቸው በመሆኑ የጋራ ትግል ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

መሰል የሰላም ግንባታ ስራዎች ደግሞ ወጣቱን በይበልጥ ተሳታፊ ማድረግ እንዳለበት ጠቅሰው፤ በተለይ አባቶች ትክክለኛውን ታሪክ ለትውልድ በማስተላለፍ ለሰላም ግንባታ በሚደረገው ጥረት አጋዥ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም