የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለእጀባ ለበረራ ደህንነትና ቁልፍ የመሰረተ ልማቶችን ለመጠበቅ የሰው ኃይሉን በተከታታይ ስልጠናዎች እያበቃ መሆኑ ተገለጸ

215


አዲስ አበባ ግንቦት 23/2015(ኢዜአ)፦የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሀገር መሪዎችን፣ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ከአደጋ የመጠበቅና የበረራ ደኅንነትን የማረጋገጥ ተልዕኮውን በብቃት ለመፈጸም የሰው ኃይሉን በተከታታይ ስልጠናዎች እያበቃ መሆኑን ገለጸ።


የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለሪፐብሊካን ጋርድና ለአገልግሎት መስሪያ ቤቱ እጀባ ፣ለበረራ ደኅንነት መኮንኖችና አመራሮች ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና ያጠናቀቁ ሰልጣኞችን አስመርቋል።



አገልግሎቱ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ እንዳመለከተው በትብብርና በአጋርነት አብረውት ከሚሰሩ የውጭ መረጃና ደኅንነት ተቋማት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ ስልጠና በዋናነት በቪአይፒ ደኅንነት ጥበቃ፣ በፈንጂ ምህንድስና ፣በድሮን አጠቃቀም ቅየሳና የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ነው። 


የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በምረቃው ላይ እንደገለጹት አደጋ መቼና እንዴት እንደሚከሰት በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም በማያቋርጥ ስልጠናና ልምምድ ብቁና ሁሌም ዝግጁ ሆኖ መገኘት አስፈላጊ በመሆኑ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ የዚህ አይነቱን ስልጠና አዘጋጅቷል። 

በመሆኑም አገልግሎት መስሪያ ቤቱ የሀገር መሪዎችን ፣ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ከአደጋ የመጠበቅ እንዲሁም የበረራ ደኅንነትን የማረጋገጥ ተልዕኮዎችን ለመፈጸም የሰው ኃይሉን በተከታታይ ስልጠና እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።


ሰልጣኞችም በስልጠና ወቅት በንድፈ ሃሳብ፡ በተግባርና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስልጠና ማግኘታቸው ለተቋማዊ ተልዕኮ ስኬታማ አፈፃፀም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።


 


የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው የቪአይፒ ደኅንነት ጥበቃ መኮንኖች ከፍተኛ ደኅንነታዊ አንድምታ ያላቸውን ግለሰቦች ደኅንነት ለመጠበቅ ተገቢውን ዕውቀት ፣ ክህሎት፣ አስተሳሰብ እና ስነምግባር ሊጨብጡ ይገባል ብለዋል። 



እያንዳንዱ የቪአይፒ ደኅንነት ጥበቃ ስምሪት ሊያጋጥሙ ከሚችሉ እንዲሁም ከሚገመቱና ካልተጠበቁ ስጋቶች እና ጥቃቶች የሀገር መሪዎችን፣ ቁልፍ የመሰረት ልማት ተቋማትን በብቃት ለመከላከል የሚያስችል የተሟላ ዕቅድ አዘጋጅቶ የመሰማራት ባህልን ማዳበር እንደሚገባ ገልጸዋል።


በብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በንድፈ-ሃሳብና በተግባር የተሰጠውን ስልጠና የተከታተሉ ሰልጣኞችም ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በተግባር ልምምድ ማሳየታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም