የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር ረቂቅ አዋጅ ተሻሽሎ እንዲቀርብ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር ረቂቅ አዋጅ ተሻሽሎ እንዲቀርብ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2015 (ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር ረቂቅ አዋጅ ተሻሽሎ እንዲቀርብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሰረት ረቂቅ አዋጁን አዘጋጅቶ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣንና የሌሎችም ባለድርሻ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በዛሬው እለት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቧል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ የረቂቅ አዋጁን ይዘትና አስፈላጊነት ጭምር ለቋሚ ኮሚቴው በዝርዝር አስረድተዋል።
የአዋጁ መዘጋጀት የተቋማትን የቴክኖሎጂ ትስስር በማጠናከር የእውቀት ሽግግር ለማድረግ የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡
የጋራ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለማካሄድ፣ የማማከር አገልግሎት ለመስጠት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የተግባር ልምምድ ለማድረግም እንዲሁ።
ኢንዱስትሪዎች ከከፍተኛ ትምህርት፣ ከቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ ከምርምር ተቋማት ጋር ያላቸውን አጋርነትና ትስስር ለማሳደግም ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን ዶክተር ሳሙኤል አስረድተዋል።
የባለድርሻ አካላትን ግዴታና ኃላፊነት በግልጽ እና በሕግ በመደንገግ ተጠያቂነትን ለማስፈንም የላቀ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ከሌላ አዋጅ ጋር የሚጣረስ ሃሳብ አለው፤ የስሙ ስያሜም የባለድርሻ ተቋማት አካታችነት ይጎለዋል፤ የሥራ ሽሚያ አለበት የሚሉና ሌሎችም ጥያቄና አስተያየቶች ከባለድርሻ ተቋማት ተነስተዋል።
በምክር ቤቱ የሰው ኃብት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፤ የረቂቅ አዋጁ መዘጋጀት አስፈላጊ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በመሆኑም ከቋሚ ኮሚቴ አባላትና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተነሱ ጠቃሚ ግብአቶችን በማካተት የዳበረ ረቂቅ አዋጅ ለግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም እንዲያቀርብ አሳስበዋል፡፡