የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራረመ

398

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሀገር በቀል የስፖርት ትጥቅ አምራች ከሆነው ጎፈሬ  ድርጅቱ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

በስምምነቱ መሰረት ኩባንያው በሁሉም እድሜ እርከን ለሚመረጡ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች የስፖርት ትጥቅ ያቀርባል።


 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን ስምምነቱ ለአራት ወራት የሚቆይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ትጥቁ ለገበያ ከሚቀርብበት ዋጋ 50  በመቶ ቅናሽ እንደሚያገኝ አስታውቀዋል።

የጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን ኩባንያቸው ከዚህ በፊት ከ17 ዓመት በታች  ለሆኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና ለዋናው ብሄራዊ ቡድኑ የስፖርት ትጥቅ ሲያቀርብ እንደነበረ አስታውሰዋል።

ይህን ተከትሎ አሁን ላይ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን የስፖርት ትጥቅ ለማቅረብ ስምምነት በማድረጋቸው ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል ።

በስምምነቱ መሰረት ኩባንያው በአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ተሳትፎ እያደረገ ለሚገኘው ዋናው ብሄራዊ ትጥቅ ያቀርባል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ብሄራዊ ቡድኑ በመጪው ሰኔ  ወደ አሜሪካ በማቅናት ለሚያደርገው የወዳጅነት ጨዋታ የጎፈሬ ምርቶችን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል ።

ጎፈሬ የምርቱን ጥራት በማሻሻል አሁን ላይ ከሀገር ውስጥ ባለፈ ከተለያዩ  የውጭ ክለቦች ጋር ስምምነት በማድረግ የስፖርት ትጥቅ እያቀረበ እንደሆነ ገልጸዋል ።

በስምምነቱ መሰረት ኩባንያው ለብሄራዊ ቡድኑ ጨዋታና የመለማመጃ የስፖርት ትጥቆችን ያቀርባል ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም