አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር ሥርዓትን በመዘርጋት ተወዳዳሪ ለመሆን ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ትብብሩን አጠናክሮ ይቀጥላል - ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና 

345

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2015 (ኢዜአ) አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር ሥርዓትን በመዘርጋት ተወዳዳሪ ለመሆን ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ትብብሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ተናገሩ። 

ኢትዮ-ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር  የቴሌ-ብር አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች የዲጂታል አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ሥምምነት አድርጓል። 

ሥምምነቱን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ፈርመውታል። 

ሥምምነቱ በዩኒቨርስቲው የሚገኙ 18 ካምፓሶች ከፍተኛ ፍጥነት ባለው ኢንተርኔት ማገናኘት፣ ስማርት ክፍሎችን መገንባትና የተለያዩ የዲጂታል አገልግሎቶችን ማቅረብ ይገኝበታል።

የብሮድ ባንድ ኢንተርኔት አቅርቦት፣ የእውቀት ሽግግርና የልምድ ልውውጥ ማድረግ፣ የምርምርና ፈጠራ ሥራዎችን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችንና የመሰረተ-ልማት ግንባታዎችን ማከናወንም እንዲሁ።

ያም ብቻ ሳይሆን ሥምምነቱ ተማሪዎች የትምህርት ክፍያቸውን በቀላሉ በቴሌ-ብር በኩል መፈጸም የሚያስችል መሆኑም ነው የተጠቀሰው።  

በተለይም የቴሌ-ብር አገልግሎት ነባርና አዲስ ተመዝጋቢ ተማሪዎች የምዝገባ፣ የፈተና የማመልከቻ፣ የሰነድ ማረጋገጫና ሌሎች ክፍያዎችን ካሉበት ቦታ ሆነው መፈጸም ያስችላቸዋል ተብሏል። 


 

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኩባንያው ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሁሉም ረገድ እየሰራ ነው።

በተለይም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእውቀት ማመንጫና የምርምር ተቋም እንደመሆኑ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚ ማዕከል እንዲሆን ቴሌኮሙ ቀጣይነት ያለው ሥራ በጋራ ይሰራል ብለዋል።

በመሆኑም ዩንቨርሲቲው በዋና ተልዕኮው ላይ ትኩረት በማድረግ ሲሰራ ቴሌኮሙ ደግሞ በዲጂታል ግንባታ ከዩንቨርሲቲው ጎን ይሆናል ነው ያሉት። 


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው የአገራት ብልጽግናና እድገት የሚደገፈው በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ዩንቨርሲቲው ብቃት ያለው የተማረ የሰው ኃይልን ለማፍራት በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም የመማር ማስተማር ሥርዓትን በመዘርጋት ተወዳዳሪ ለመሆን  ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከኩባንያው ጋር የስማርት ክፍሎችን እውን ያደረገ ሲሆን፤ የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚነቱን እያሰፋ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የትምህርት ተቋም ለመሆን ይሰራል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ተቋማት በድህረ ምረቃ የትምህርት መርሃ ግብር በቴሌኮሙኒኬሽን ኔትዎርክ ኢንጂነሪንግና የቴሌኮሚዩኒኬሽን ኢንፎርሜሽን ሲስተም የሙያ መስኮች የጋራ ሥርዓተ-ትምህርት ቀርጸው ወደ ሥራ ገብተዋል። 

ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን አጋርነት ይበልጥ በማጠናከር በአገሪቱ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሳለጥ በጋራ እንደሚሰሩ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም