ቀጥታ፡

በደቡብ ኦሞ ዞን የመስህብ ስፍራዎችን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ 17 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

ጂንካ ግንቦት 23 / 2015 (ኢዜአ).፡-  በደቡብ ኦሞ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት የመስህብ ስፍራዎችን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

ገቢው የተገኘው በዞኑ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከጎበኙ ከ150 ሺህ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ   ቱሪስቶች መሆኑን መምሪያው ገልጿል።

በመምሪያው የፕሮጀክት ጥናትና ሀብት ማፈላለግ ማርኬቲንግ ቡድን መሪ አቶ ሞገስ አየለ እንዳመለከቱት፤ ዞኑ ቱሪስቶች ሊጎበኟቸው የሚችሉ  የበርካታ ባህላዊ፣ታሪካዊ እና ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦች መገኛ ነው።


 

የቱሪስት መስህብ ከሆኑት ጸጋዎች መካከል የሐመር ባህላዊ አጋጌጥ፣አለባበስና ውበት መጠበቂያ ስነ-ዘዴዎች፣ኢቫንጋዲ የምሽት ጭፈራ፣በጋብቻ ወቅት ጥንካሬን ለመግለፅ የሚደረግ የከብት ዝላይ  ክዋኔዎችን እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

እንዲሁም የቦዲ ማህበረሰብ የባለፀግነት መገለጫ የውፍረት ውድድር "ኬኤል" የሙርሲ- የዱላ ምክክቶሽ "ዶንጋ" የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ ትዕይንቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

 በዞኑ የ16 ብሔረሰቦች አለባበስ፣ አጋጌጥ፣ አመጋገብ፣ የሙዚቃ ስልትና የአኗኗር ዘይቤም ሌላው የቱሪስት መስህብ መሆናቸውን  አመላክተዋል።


 

በኦሞና በማጎ ብሔራዊ ፓርኮች  የሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንሰሳት፣ በዞኑ የሚገኙ የተፈጥሮ ዋሻዎች፣ ፏፏቴዎችና የሎኩላን የተፈጥሮ ፍል ውሃ፣ የውልሸት የአደን ጣቢያና የታችኛው የኦሞ ሸለቆ መካነ ቅርስ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦች እንደሆኑም አብራርተዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ150 ሺ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ  ቱሪስቶች እነዚህን የመስህብ ስፍራዎች እንደጎበኙ አስታውቀዋል።

ለቱሪስቶቹ አገልግሎት የሰጡ ድርጅቶችና ተቋማትም ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን  አቶ ሞገስ አስታውቀዋል።

በቀጣይም የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ በዞኑ የሚገኙ መስህቦችን የመጠበቅ፣የመንከባከብና በ"ዲጅታል ፕላት ፎርም" አማካኝነት የማስተዋወቅ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እንደ መንገድ ያሉ መሰረተ-ልማቶች ባልተሟሉበት አካባቢዎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለመገንባት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የጂንካ ከተማ የቱሪስት መዳረሻ ብትሆንም ስታንዳርድ የጠበቁ በቂ ሆቴሎች ባለመኖራቸው የእንግዶችን ቆይታ ጊዜ በማራዘም ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት  በሐመር ወረዳ ቱርሚ ከተማ የተገነቡ ሎጆች ለቱሪስቶች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቁመው ፤የግል ባለሀብቶች ጂንካን ጨምሮ በሌሎች የዞኑ አካባቢዎች ሎጆችንና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን ቢገነቡ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመልክተዋል ።

ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሚገኘውን ሀብት ለማህበረሰብ ልማት ለማዋል በትኩረት እየተሰራ እንዳለም ጠቁመዋል ።

በጂንካ ከተማ በቱር አፕሬተርና በአስጎብኚነት ሙያ ላይ የተሰማራው ወጣት አዲስ-አለም ሀብታሙ በሰጠው አስተያየት፤በዞኑ ያሉ የቱሪስት መስህቦችን ለተለያዩ ሀገራት ዜጎች ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

ሌሎችም አስጎብኚዎች የሀገሪቱን  ገፅታ በማጉላትና ስለ መስህቦች ትክክለኛ መረጃ በመስጠት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁሟል ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም