በኦሮሚያ ክልል ሰላምን ለማረጋገጥ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው--አቶ ሃይሉ አዱኛ

240

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2015(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ሰላምን ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ ገለጹ።

ሃላፊው ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ኢትዮጵያ የተለያየ እምነት ተከታዮች ተከባብረው የሚኖሩባት እንደመሆኗ የክልሉ መንግስትም በሃይማኖት እኩልነት የሚያምንና እውቅናም የሚሰጥ ነው።

አንዳንድ አካላት በኦሮሚያ ክልል ህገ ወጥ ግንባታዎችን የማፍረሱን ሥራ በአንድ ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ማስመሰላቸው ፈጽሞ ትክክል አለመሆኑን አቶ ሃይሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም የሕገ-ወጥ ቤቶች ፈረሳ ሒደት መስጅድ ላይ ያተኮረ አለመሆኑንና በክልሉ 600 በሚሆኑ ከተሞች በህገ-ወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶችን የማፍረስ ሒደት እንደሚከናወን ገልጸዋል።

ሕግ የማስከበር ስራውም በዋናነት ህገ-ወጥነትን በዘላቂነት ለመከላከል ያለመ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በቀጣይም የክልሉ መንግስት በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ በማረጋገጥ የሃይማኖት ተቋማት እና የእምነቱ ተከታዮችም እምነትን ተገን አድርገው ሁከት እና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን በጋራ እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም