ኢትዮ ቴሌኮም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የዲጂታል አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

275

አዲስ አበባ ግንቦት 23 /2015(ኢዜአ):-ኢትዮ ቴሌኮም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የዲጂታል አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ስምምነት ዛሬ ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ  ፍሬህይወት ታምሩ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ናቸው።

ስምምነቱ ኢትዮ ቴሌኮም በዩኒቨርሲቲው የቴሌ ብር አገልግሎትን ጨምሮ የ’ኮኔክቲቪቲ’ እና ዲጂታል አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው ነው።

አገልግሎቱ 18 ካምፓሶች ከፍተኛ ፍጥነት ባለው ኢንተርኔት ማገናኘት፣ ስማርት ክፍሎችን መገንባት፣ የእውቀት ሽግግርና የልምድ ልውውጥ ማድረግ፣ የምርምርና ፈጠራ ስራዎችን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችንና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናወን እንዲሁም ተማሪዎች የትምህርት ክፍያቸውን በቀላሉ በቴሌ ብር በኩል መፈጸም የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ኩባንያው ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእውቀት ሽግግር የሚካሄድበት ስፍራ በመሆኑ በቴክኖሎጂ እና ‘ኮኔክቲቪቲ’ በማገዝ በሚጠበቅበት ልክ ውጤታማ እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው፣ የተማረ የሰው ኃይል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከኩባንያው ጋር የስማርት ክፍሎችን እውን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚነቱን በማስፋት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የትምህርት ተቋም ለመሆን በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም