የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ የሰዓት ማስተካከያ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ የሰዓት ማስተካከያ ተደረገ
አዲስ አበባ ግንቦት 23 2015(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ በ27ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ የሰዓት ማስተካከያ ማድረጉን አስታወቀ።
የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም መደረግ ይጀምራሉ።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ በሃዋሳ ከተማ አመሻሽ ላይ እየጣለ በሚገኘው ዝናብ ምክንያት የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የሚጀምሩበት ሰዓት ላይ ማስተካከያ ማድረጉን ገልጿል።
በዚሁ መሰረት በ9 ሰዓት እንዲጀምሩ ፕሮግራም የወጣላቸው ጨዋታዎች በሙሉ 7 ሰዓት እንዲሁም በ12 ሰዓት ይጀምሩ የነበሩ ጨዋታዎች ደግሞ 10 ሰዓት ላይ እንደሚጀመሩ አመልክቷል።
በተጨማሪም ጨዋታው ተጀምሮ በዝናብ ምክንያት የተቋረጠ ጨዋታ ካለ ጨዋታው በማግስቱ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ በሃዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ላይ እንዲጠናቀቅ ኮሚቴው ውሳኔ አስተላልፏል።