ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቻይና ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያና የቻይና ወዳጅነትና ትብብርን ከፍ ያደረገ ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

247

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2015(ኢዜአ):-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቻይና ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያና ቻይና ወዳጅነትና ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፤ በውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ መስክ በሳምንቱ በተከናወኑ አበይት ጉዳዮች ላይ በማተኮር መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከግንቦት 15 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም በቻይና ይፉዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የጉብኝቱ አላማ የአገራቱን አገሮች የትብብር ግንኙነትና ወዳጅነት ማጠናከርን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በቻይና ጉብኝታቸው ከተለያዩ የአገሪቷ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር ሁሉን አቀፍ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር በሁሉም መስክ በትብብር ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገራቸውን አምባሳደር መለስ ተናግረዋል።

በቻይና የሁለቱን አገራት የንግድ ትስስር የሚያጎለብት የንግድና ኢንቨስትመንት መድረክ በጉብኝታቸው ወቅት መካሄዱንም ጠቅሰዋል።

የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉበኝት የኢትዮ-ቻይናን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያን ታሪክና ስልጣኔ በሚመጥን መልኩ በቻይና የኢትዮጵያ ኢምባሲ በነበረበት ቦታ በአዲስ መልክ ተገንብቶ መመረቁንም ገልጸዋል።

የኢትዮ ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እ.አ.አ በ1970 ሲሆን በቀጣዩ ዓመትም  የየአገራቱ ኢምባሲዎች በአዲስ አበባና ቤጅንግ መክፈታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተጠናከረ መጥቶ ከ2006 ጀምሮ ቻይና የኢትዮጵያ ዋነኛ የንግድ አጋር መሆን ችላለች።

በኢንቨሰትመንት መስክም በርካታ የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት መስኮች  ሙአለንዋያቸውን በማፍሰስ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም