ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የስነ ሕዝብና ተያያዥ የልማት ጉዳዮችን በልማት እቅዶቿ ውስጥ አካታ እየተገበረች ነው - አቶ ሳንዶካን ደበበ 

 

አዲስ አበባ ግንቦት 23 /2015(ኢዜአ):-ኢትዮጵያ የስነ ሕዝብ እና ተያያዥ የልማት ጉዳዮችን በልማት እቅዶቿ ውስጥ አካታ እየተገበረች እንደምትገኝ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳንዶካን ደበበ ገለጹ።

የዓለም ስነ-ሕዝብ የ2023 ዓመታዊ ሪፖርት ትናንት ማምሻዉን በኢትዮጵያ ይፋ ሲሆን ሪፖርቱን የተመለከተ ውይይትም ተደርጓል።


 

በመርሐ-ግብሩ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳንዶካን ደበበ፣የተባበሩት መንግስታት የስነ ሕዝብ ፈንድ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኮፊ ካውሜ እንዲሁም የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቢባቱ ዋኔ-ፎል እና ሌሎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ሪፖርቱ “8 ቢሊዮን ሕይወት ፣ ማለቂያ የሌላቸዉ አማራጮች የመብትና የምርጫ ጉዳይ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳንዶካን ደበበ ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ካላቸው 14 የዓለም አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።

መንግስት የሕዝብ ቁጥር የሚያመጣውን መልካም እድልና ተግዳሮት ጠንቅቆ እንደሚረዳና በ10 ዓመት እቅዱ ከዘላቂ የልማት ግቦች እና ከአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣመ እንዲሆን መደረጉን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የስነ ሕዝብና ተያያዥ የልማት ጉዳዮችን በልማት እቅዶቿ ውስጥ አካታ እየተገበረች መሆኑን ተናግረዋል።

ስለ ስነ ሕዝብ መወያየት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱን ሰው በተለይም የሴቶችና ሕጻናትን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት አቶ ሳንዶካን።

መንግስት የስነ ሕዝብ ፖሊሲን መከለስና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን እየተገበረ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም