ዋናውን የምክክር ሂደት በቀጣይ ዓመት ለመጀመር የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

277

ሚዛን አማን፣ ግንቦት 23 / 2015 (ኢዜአ):- አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበትን ዋናውን የምክክር ሂደት በሚቀጥለው ዓመት ለመጀመር የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

ኮሚሽኑ ሰሞኑን በተለያዩ ክልሎች የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ ምልመላ ሂደት እና አጀንዳ ማሰ ባሰብ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሲሰጥ በነበረው ስልጠና ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ምንም አይነት አጀንዳ ወደ ኋላ እንዳይቀር በጥንቃቄ እየተመራ ነው ብለዋል።

በሚቀጥለው ዓመት ወደ ምክክር ለመግባት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሁሉም መዋቅሮች ከተለያዩ አደረጃጀቶች ተሳታፊዎችን የሚመለምሉ ሰባት  ተባባሪ አካላት የተመረጡ ሲሆን ግልጽ አካታችና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን መልማዮች ተገቢውን ስልጠና ወስደዋል ነው ያሉት።


 

በሚመለመሉ ተሳታፊዎች በኩል የሚሰበሰቡ ሀገራዊ የህዝብ አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ምክር ቤት ደርሰው ለምክክር ይቀርባሉ በማለት ገልጸው፤ የአካባቢ አጀንዳዎች በመዋቅር ደረጃ እንዲፈቱ እናመቻቻለን ብለዋል።

ሀገራዊ አጀንዳ አለኝ የሚል ማንኛውም አካል ሀሳቡ እንዳይቀርበት በአደረጃጀት በኩል ከመስጠት ባለፈ በስልክ፣ በአካልና ሌሎች የሀሳብ ማቅረቢያ መንገዶች ለኮሚሽኑ እንዲሰጥ አመቻችተን እየተቀበልን ነው ሲሉ አክለዋል።

ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሔው መወያየት መሆኑን ገልጸው፤ ለመወያየት ደግሞ በተገቢው መንገድ መደማመጥ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በቦንጋ ከተማ በተካሄደው የአጀንዳ አሰባሰብ እና የተሳታፊ ምልመላ ስልጠና ከወሰዱ ተባባሪ አካላት መካከል ከዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ የተገኙት አቶ ዳዊት ወንድሙ በሰጡት አስተያየት ለምክክሩ ስኬት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ችግሮችን ለመፍታት ምንጩን ማወቅ ተገቢ በመሆኑ ህብረተሰቡ በአግባቡ አጀንዳውን ለምክክር ኮሚሽኑ ማቅረብ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ከካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ የተገኙት መምህርት ጥሩነሽ ወንዳፍራሽ በበኩላቸው የመወያየትና ችግሮችን በጋራ የመፍታት ባህል አለን ሲሉ ገልጸዋል።

ምክክሩ በዚህ አግባብ የሚፈጸም መሆኑ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ ዕድል እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዘር፣ ከፖለቲካና ከእምነት መሰል ተጽዕኖዎች ነጻ የሆኑ አካላት በምክክር ኮሚሽኑ ውይይት እንዲሳተፉ በጥንቃቄ የምልመላውን ሂደት እንሰራለን ብለዋል።

በጥቃቅን ጉዳዮች የሚፈጠር ግጭት ያስከተለብን ጉዳት ቀላል ባለመሆኑ በምክክሩ ተነጋግረን በመግባባት ሀገራችንን ወደ ፊት ማራመድ አለብን ያሉት ደግሞ ከቤንች ሸኮ ዞን የተሳተፉት አቶ ብርሃኑ ገብረመድኅን ናቸው።

በውይይት ችግሮችን የመፍታት ባህላችን መሸርሸሩ ያስከተለብንን ቀውስ አሁን እየተፈጠረ ባለው የምክክር መድረክ ለመፍታት ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም