የስፖርት ክለቦች የራሳቸውን ገቢ እንዲያሳድጉና ለሀገር ልማት በጎ ሚና እንዲጫወቱ በጥናትና ምርምር ማገዝ ይገባል--የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ክለቦች የራሳቸውን ገቢ እንዲያሳድጉና ለሀገር ልማት በጎ ሚና እንዲጫወቱ በጥናትና ምርምር ማገዝ ይገባል--የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 22/ 2015 (ኢዜአ) የስፖርት ክለቦች የራሳቸውን ገቢ እንዲያሳድጉና ለሀገር ልማት በጎ ሚና እንዲጫወቱ በጥናትና ምርምር ማገዝ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ስምንተኛውን ዓመታዊ የስፖርት ጥናትና ምርምር ጉባዔ ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።
የአካዳሚው የጥናትና ምርምር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አመንሲሳ ከበደ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ስፖርት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አበርክቶ አለው።
በጉባዔው የስፖርት ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ልማት ያለው አበርክቶ፣ በአትሌቲክስ ግንባታና አስተዳደር እንዲሁም የስፖርት ሕክምና ነክ ጉዳዮች የሚመለከቱ ጥናቶች መቅረባቸውን ተናግረዋል።
በስፖርቱ መስክ ከሚንቀሳቀሱ ክለቦች መካከል በገቢ ራሳቸውን ባለመቻላቸው ምክንያት ደመወዝ ካለመክፈል እስከ መፍረስ የደረሱ መኖራቸውን በመጥቀስ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ በምርምር የተደገፉ መፍትሔዎች ለክለቦችና ለዘርፉ ባለድርሻ አካላት እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።
ክለቦች የገቢ አቅማቸውን ለማሳደግ ከጥገኝነት የተላቀቀና ትርፋማ የገቢ አማራጭን እንዲከተሉ ማድረግ የግድ መሆኑን አንስተዋል።
የስፖርት ጥናትና ምርምሮች የአመላከከት ለውጥ ለማምጣትና የስፖርቱ ተቋማት የገቢ አማራጮችን በማስፋት ለሀገር ኢኮኖሚ ልማት በጎ ሚና እንዲኖራቸው ስለሚያደርጉ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።
ለዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ ተሞክሮዎችን ቀምሮ ከሀገራዊ አውዱ አንጻር በመተንተን ምክረ ሀሳቦችን ማመላከትና ለተግባራዊነቱ መስራት እንደሚገባ ነው ያብራሩት።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚም እንደ ተቋም የስፖርቱን ዘርፍ ለማሳደግና የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በጥናትና ምርምር መስክ በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘርፉ ላይ ለሚደረጉ ምርምሮች ትኩረት እየሰጡ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ተጠናክሮ መጠቀል እንዳለበት ተናግረዋል።