ቀጥታ፡

"የፒያኖዋ እመቤት" እማሆይ ፅጌማርያም ገብሩ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚዘክር መርሐግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ)፦ "የፒያኖዋ እመቤት" እማሆይ ፅጌማርያም ገብሩ በሕይወት ዘመናቸው ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚዘክር መርሐግብር በእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተካሂዷል።

ለዘርፉ ያደረጉትን አበርክቶ በማስመልከት የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሙዚቃ ትምህርት ክፍል በስማቸው ተሠይሟል።

በመርሐግብሩ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር  ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ የቀድሞ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሰብሳቢ አርቲስት ደበበ እሸቱ እንዲሁም አንጋፋና ወጣት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።


 

በመድረኩ የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ተሾመ ፈይሳ የመርሐግብሩ ዋና አላማ ለእማሆይ ፅጌማርያም ገብሩ መታሰቢያና ምስጋና ማቅረብ ነው ብለዋል።

እማሆይ ፅጌማርያም ገብሩ ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፍ ያሳረፉት አሻራ የገዘፈ ነው በማለት ጠቅሰው ይህም መርሐግብር ስራቸውን ለመዘከር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በስማቸው የተቋቋመው ምግባረ ስናይ ድርጅት ለኮሌጁ የሙዚቃ ትምህርት ክፍል የሙዚቃ መሳሪያዎችን ድጋፍ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል።

የቀድሞ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሰብሳቢ አርቲስት ደበበ እሸቱ እማሆይ ፅጌማርያም ገብሩ ቁምነገረኛና መካሪ ሰው እንደነበሩ አውስቷል።

የእማሆይ ፅጌማርያም ሥራዎች በወረቀት ላይ ብቻ ሰፍረው የሚነገሩ ሳይሆን በሰዎች አእምሮ ታትሞ የሚቀር ነው በማለት አመልክቷል።


 

አርቲስት ደበበ የእማሆይ ፅጌማርያም የሙዚቃ ቅንብር ክላሲክ የሚባለው የሙዚቃ ዘርፍ ዕንቁ ነው በማለት ገልጿል።

በኢትዮጵያ ቀዳሚዋ የቫዮሊን እና ፒያኖ አቀናባሪ የነበሩት እማሆይ ፅጌማርያም ገብሩ ባሳለፍነው መጋቢት ወር ማረፋቸው ይታወሳል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም