የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አመራሮች እና ከፍተኛ ሰልጣኝ መኮንኖች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉብኝት አደረጉ

265

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ) ፦የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አመራሮች እና ከፍተኛ ሰልጣኝ መኮንኖች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉብኝት አድርገዋል።

የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን መልዕክት የጽህፈት ቤታቸው ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ያቀረቡ ሲሆን፤ የአገር መከላከያ ሰራዊት በሁሉም አውዶች የአገርን ደህንነት እና ሉዓላዊነት ከጥቃት ለመጠበቅ ከሕዝብ አብራክ ወጥቶ ለሕዝብ እየኖረ ያለ የዜጎች አለኝታ በመሆኑ ላቅ ያለ ክብር የሚገባው ነው ብለዋል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና መከላከያ ሰራዊት የአገር እና የሕዝብ መከታ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ቡልቲ ታደሰ በበኩላቸው ኮሌጁ በሰው ኃይል ግንባታ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር እና ስልጠናዎችን በመስጠት በሰው ኃይል ግንባታ ብቁ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ሰራዊቱ በዓለም ሰላም ማስከበር እና በሌሎች ተልኮዎች ውጤታማነቱን ማስመስከሩን ገልጸው ኮሌጁ በቀጣይም ስራውን በተሻለ ተግባር እንዲከውን የሚያስችል ስልጠና እየሰጠ ነው ብለዋል ።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲቲዩት የፖለቲካ ሳይንስ መሪ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዳር እስከዳር ታዬ “የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ትናንት እና ዛሬ” በሚል የመወያያ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም