በመዲናዋ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና የአገልግሎት መቆራረጥ ችግርን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና የአገልግሎት መቆራረጥ ችግርን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ  መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና አገልግሎት መቆራረጥ ችግርን ለመቅረፍ የፌዴራል እና የከተማ አስተዳድሩ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች በተገኙበት ውይይት ተካሄዷል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል እና ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ያለባት ከተማ በመሆኗ፤ ደረጃዋን የሚመጥን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በሰው ሰራሽና በተፈጥሯዊ ምክንያቶች በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርስን ጉዳት በኃይል አቅርቦት ላይ መቆራረጥ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።

የኃይል መቆራረጥ በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይም ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጸው፤ ከተማ አስተዳድሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋፋት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን እያስፋፋ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው አዲስ አበባን ጨምሮ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማሻሻል አስቻይ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በአዲስ አበባ ከመሰረተ ልማት እድገቷ ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ ፍላጎትን ለማሳደግና ለማዘመን ከፍተኛ በጀት ተመድቦ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለአብነትም ከሰው ንክኪ ነጻ ቆጣሪዎችን ለኢንዱስትሪ ደንበኞች መቅረቡን እና ደንበኞች ቅሬታቸውን በቴክኖሎጂ ተጠቅመው በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያቀርቡበት ስርዓት መዘጋቱን አንስተዋል።

በሌላ በኩል የአገልግሎት ለማሳለጥና ከከተማ አስተዳድሩ ጋር በቅርበት ለመስራት ያልተማከለ አደረጃጀት መፍጠሩንም ነው አቶ ሽፈራው ያስረዱት።

የኃይል መቆራረጥ ችግር ከመቅረፍ ባሻገር የኃይል አቅርቦት እና አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባችው የመዲናዋ አካባቢዎች አገልግሎቱን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የዘርፉን ችግሩን ለማቃለል የሚያስችል የ90 ቀናት እቅድ የሚያወጣ ቡድን ተቋቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም