ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና በሰዎች የመነገድ ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የባለድርሻ አካላት የትብብር ጥምረት ሊጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ

208

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ)፡- ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና በሰዎች የመነገድ ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የባለድርሻ አካላት የትብብር ጥምረት ሊጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በሚመለከት በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ ተግባራትን ማስፋት የሚያስችል አገር አቀፍ የልምድ ልውውጥ መድረክ ተካሂዷል።

የልምድ ልውውጥ መድረኩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በአማራ ክልል መካከል የተከናወነ ሲሆን፤ በቀጣይም ወደ ሌሎች ክልሎች እንደሚሰፋም ተጠቁሟል፡፡


 

በመረሓ-ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ፣ የከተማዋ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ እና የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ገረመው ገብረፃዲቅ ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የምክር ቤት አባላት እንዲሁም የአማራ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ፤ በኢትዮጵያ ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር፣ በሰዎች የመነገድና በህገ ወጥ መንገድ ለውጭ አገራት የስራ ስምሪት ዜጎችን የመላክ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ዘርፈ ብዙ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

ይህንን ተግባር በማጠናከር ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘርፉ ከሚሰሩ አጋር አካላት ጋር የትብብር ጥምረት ማቋቋሙን አንስተዋል።

ጥምረቱ በከተማዋ ፍትህ ቢሮ፣በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተዋቀሩበት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ጥምረቱ የሰዎች ዝውውር በስፋት የሚፈፀሙባቸው አካባቢዎችን በመለየት የቁጥጥርና የክትትል ስራዎች ማከናወን ዋነኛ ተግባሩ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

በተጨማሪም በጉዳዩ ላይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማስፋትና ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ይህንን የትብብር ጥምረት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በማስፋት ወንጀሉን ማስቆምና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ተክሌ በዛብህ በበኩላቸው ከተማዋ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል በሰፋት ከሚፈጸምባቸው አካባቢዎች መካከል አንዷ መሆኗን አንስተዋል፡፡

ወንጀሉ በህጻናትና በሴቶች ላይ ጎልቶ እየተፈጸመ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በሰዎች የመነገድ፣ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ የማሻገርና ህገ-ወጥ የስራ ስምሪትን በሚመለከት  ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመፈረም ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝም ጨምረው ገልጸዋል።

የወንጀሉን አስከፊነትና በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተጽእኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት  ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑም አንስተዋል።

ይሁን አንጂ እነዚህ ወንጀሎች አይነታቸውና ሁኔታቸው እየተቀያየረ የሚፈጸሙ በመሆናቸው የመከላከል ስራውን በተሻለ ቅንጅት ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የተቋቋመውና በስራ ላይ ያለውን የትብብር ጥምረት አቅም ማሳደግና ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የማስፋትና የልምድ ልውውጥ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ገረመው ገብረጻዲቅ እንዲሁ በክልሉ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል በስፋት እንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡ 

በዚህም ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎችንና አካባቢዎችን በመለየትና ልዩ ክትትል በማድረግ ወንጀሉን የመከላከልና ተጠያቂነትን የማስፈን ስራው በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ ወንጀሉ የሚፈጸምበት ሁኔታ በእጅጉ ውስብስብ በመሆኑ የአጋር አካላት ድጋፍና እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል።

በመሆኑም ዛሬ በተደረገው የልምድ ልውውጥ የትብብር ጥምረትን ማቋቋም ያለው ጠቀሜታ የጎላ በመሆኑ ተግባሩን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም