ከሀገር ውስጥ የስኳር ምርት በተጨማሪ 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ከውጭ ለማስገባት ዝግጅት ተደርጓል- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

201

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015(ኢዜአ)፡- ከሀገር ውስጥ የስኳር ምርት በተጨማሪ 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ከውጭ ለማስገባት መንግስት በዝግጅት ላይ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የበጀት ምንጫቸውን ለብሔራዊ ባንክ አሳውቀው በራሳቸው የውጭ ምንዛሬ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ከውጭ እንዲያስገቡ ከተፈቀድላቸው ባለኃብቶች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

የዘይት፣ ስኳር እና ሌሎችም መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች እጥረትና የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር መንግስት ለሀገር ውስጥ ባለኃብቶች ፍራንኮ ቫሉታ መፍቀዱ ይታወቃል፡፡

በዚህም ባለፉት አስር ወራት 411 አስመጭዎች በፍራንኮ ቫሉታ የተሳተፉ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የዘይት አቅርቦት 85 በመቶ መሸፈን ተችሏል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በልሁ፤ መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ፍራንኮ ቫሉታ በመፍቀድና በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በታክስ መልክ ያገኘው የነበረውን 10 ቢሊየን ብር አጥቷል፡፡

በፍራንኮ ቫሉታ የሚሳተፉ አስመጭዎችን አገልግሎት ከማሳለጥ ባለፈ የሀገር ውስጥ ምርቶች በበቂ ሁኔታ እንዲቀርቡ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል ብለዋል፡፡

በመሆኑም መንግስት ለአምስት የአገር ውስጥ የተጣራ ዘይት አምራች ድርጅቶች የማምረት አቅማቸውን ታሳቢ በማድረግ 50 ሚሊየን ዶላር እንደመደበላቸው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች 650 ኩንታል ስኳር ተመርቶ ለገበያ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፤ በስኳር ኮርፖሬሽን በኩል ተጨማሪ 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ከውጭ ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ለአብነት በፍራንኮ ቫሉታ በአማካኝ በ342 ብር ወደ አገር ወስጥ የሚገባ ባለ አምስት ሊትር ዘይት የተለያዩ የግብይት ሰንሰለቶችን አልፎ ለሸማቹ እስከ 1 ሺህ ብር በሚደርስ የተጋጋነ ዋጋ እየቀረበ መሆኑ ተገልጿል።

በመሆኑም በፍራንኮ ቫሉታ ምርታቸውን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡት አስመጭዎች ቀጥታ ከሸማቹ ጋር እንዲገናኙ የቅዳሜና እሁድ ገበያን ማስፋት እንደ አማራጭ ተይዟል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባና በክልሎች እስከ 1 ሺህ ነጋዴዎችና ሸማቾች በቀጥታ የሚገናኙበት የቅዳሜና እሁድ የገበያ ሰንሰለት ለመፍጠር መልካም ጅምር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና የዋጋ ንረትን ለመግታት አቅርቦትና ፍላጎቱን የማመጣጠንና ስርጭቱን ፍትሃዊ የማድረግ ስራ በስፋት ይከናወናል በማለት ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከብሔራዊ ባንክ ዶላር የሚያገኙ ድርጅቶች ከስምንት በመቶ በላይ ትርፍ እንዳያሰሉ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በፍራንኮ ቫሉታም ሆነ በማንኛውም መንገድ ከውጭ ያስገቡትን ምርት መጋዘን ውስጥ ማከማቸት በህግ ያስጠይቃል፤ መንግስትም ተከታትሎ እርምጃ ይወስዳል ሲሉ አረጋግጠዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም