በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ማህበራዊ ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ጃፓን እንደምትደግፍ አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ

120

ዲላ ግንቦት 22/2015  (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ማህበራዊ ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የጃፓን መንግስት እንደሚደግፍ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ።

በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች አጎራባች አካባቢዎች ማህበራዊ ልማትና መስተጋብርን የሚያጎለብት ፕሮጀክት ዛሬ በዲላ ከተማ ይፋ ሆኗል።

ፕሮጀክቱ ከጃፓን መንግስት በተገኝ 83 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በቀጣይ ሦስት ዓመታት በዞኖቹ ባሉ አራት አጎራባች ወረዳዎች የሚተገበር መሆኑም ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ፕሮጀክቱ ይፋ ሲደረግ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ማህበራዊ ልማትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማገዝ የጃፓን መንግስት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።


 

በተለይ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መሰረት ይጥላል ተብሎ ለሚጠበቀው ለኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የ3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉንም ለአብነት አንስተዋል።

ዛሬ በሁለቱ ዞኖች አጎራባች አካባቢዎች ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት የዚህ ድጋፍ አካል መሆኑን ጠቅሰው፣ "ፕሮጀክቱ ለሰላም ግንባታ፣ ለማህበራዊ ኑሮ መሻሻልና ለማህበራዊ ትስስር ጠቀሜታው የጎላ ነው" ብለዋል።

በተለይ አጎራባች አካባቢዎችን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ዘላቂ ሰላም ከማስፈን ባለፈ ሴቶችና ወጣቶች ኑሯቸውን ሊያሻሽሉ በሚችሉ ስራዎች እንዲሳተፉ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ማህበራዊ ልማት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በጃፓን መንግስት በኩል መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በሁሉቱ ዞኖች አጎራባች አካባቢዎች ከዚህ ቀደም የነበረው የጸጥታ ችግር ሙሉ በሙሉ ተፈትቶ ህብረተሰቡ ፊቱን ወደልማት ማዞሩን ያነሱት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ጉጂ ዞን የፀጥታ አስተዳደር የግጭት ፈጥኖ ምላሽ አስተባባሪ አቶ አየለ ወላሳ ናቸው።

በዞኑ ገላናና ቡሌ ሆራ ወረዳዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የድርቅና የጎርፍ አደጋ ችግሮች ለማቃለል የማህበረሰብ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም መጀመሩ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ በአካባቢው የልማትና የማህበራዊ መስተጋብርን በሚያጎለብት መልኩ ተፈጻሚ እንዲሆን በዞኑ በኩል አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም ተናግረዋል።

በደቡብ ክልል የጌዴኦ ዞን ፋይናንስ መምሪያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ክትትል አስተባባሪ አቶ ከፍያለው ቢሬ በበኩላቸው፣ ሁለቱን ዞኖች በመሰረተ ልማትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውን በማጠናከር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ይህንን ከማጠናከር ባለፈ ህብረተሰቡ ሰርቶ እንዲለወጥ የፋይናንስ ድጋፍና ስልጠና በመስጠት የማህበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል አስተዋጾው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ የጃፓን ኤምባሲና የሁለቱ ዞኖች የሥራ ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ፕሮጀክቱ ከ40 ሺህ በላይ አባወራና እማወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም