በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች ህዝብን እያማረሩ ያሉ ህገ-ወጥ ጫኝና አውራጆች ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል- የአዲስ አበባ ሰላምና  ጸጥታ አስተዳደር  ቢሮ

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች  ህዝብን እያማረሩ ያሉ ህገ-ወጥ ጫኝና አውራጆች ላይ  ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ሰላምና  ጸጥታ አስተዳደር  ቢሮ አስታወቀ፡፡ 

የቢሮው  ኃላፊ ወይዘሮ  ሊዲያ ግርማ  ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ፤ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በኢ-መደበኛ መንገድ የተደራጁ ጫኝና አውራጆች  ከመጠን  በላይ  በማስከፈል እና ለህግና  ስርዓት ተገዥ ባለመሆን ህዝብን እያማረሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በተለይም  በጋራ መኖሪያ  ቤቶች አካባቢ ችግሩ በስፋት እንደሚስተዋል  ገልጸው፤ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ  የ44 ማህበራት አባል የሆኑ 505 ጫኝና አውራጆች በህግ እንዲጠየቁ መደረጉን  ተናግረዋል፡፡   

በተጨማሪም በተገልጋይ ላይ ድብደባና ሌሎችም የሰብዓዊ  መብት  ጥሰት የፈጸሙ  97 ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር  ስር መዋላቸውን  አስታውቀዋል፡፡  

በቀጣይም የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊዋ አረጋግጠዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም