በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የልማት መስኮች ስኬታማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መከናወኑ ተገለጸ

102

ግምቢ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በተለያዩ የልማት መስኮች ስኬታማ የበጋ ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መከናወኑን የዞኑ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የዞኑ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተገኝ ቀኖ ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በተለያዩ መስኮች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲከናወን ቆይቷል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተካሄደ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

የዞኑ በጎ ፈቃደኞች ከ45 በላይ በሆኑ የልማት ዘርፎች ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ በዚህም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

ከእነዚህም፤ በመንግስትና በበጎ ፈቃደኛ ባለሀብቶች ትብብር 136 አነስተኛ ድልድዮች መሰራታቸውንና የ290 የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳትና አዲስ ግንባታ ስራ መከናወኑን እንደ አብነት አንስተዋል።


 

በዞኑ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ቤተ-መጻህፍት የሚውሉ የተለያዩ ይዘት ያላቸው ከ95 ሺህ በላይ መጻህፍት ከበጎ ፈቃደኞች መሰብሰቡንም አክለዋል። 

በተጨማሪም በዞኑ ገጠር አካባቢዎች 300 የመምህራን ቤቶች እድሳት እንዲሁም የቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ መከናወኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍና የደም ልገሳም በበጎ ፈቃደኞቹ የተከናወኑ ስራዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።


 

በበጎ ፈቀደኞች የተሰሩ የልማት ስራዎችም መንግስት ለሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች አጋዥ በመሆናቸውም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመጪው ክረምትም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የዜግነት የበጎ ፈቃድ ስራዎች ተጠናክረው የሚከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ ስራው እየተሳተፉ ካሉ የዞኑ ነዋሪዎች መካከል የግምቢ ከተማ ነዋሪው ሼህ ሀሰን መሓመድ በበጎ ፍቃድ ስራው የህሊና እርካታ ማግኘታቸውን ገልጸው ሌሎችም በበጎ ፈቃድ ስራ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

ሌላው ተሳታፊ አቶ አብደላ አብዱ በበኩላቸው ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ለአቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች የአልባሳት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በመጪው ክረምት ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመሳተፍ ዝግጅት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም