የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አመራርና ሠራተኞች የግብርና ሳይንስ ኤግዚቢሽንን ጎበኙ

129

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015(ኢዜአ)፡- የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አመራርና ሠራተኞች በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የግብርና ሳይንስ ኤግዚቢሽን ጎበኙ።

"ከቤተ-ሙከራ ወደ አዝመራ" በሚል መሪ ሃሳብ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የግብርና ሳይንስ ኤግዚቢሽን ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ለተመልካቾች ክፍት መደረጉ ይታወቃል።

በአውደ-ርዕዩ ላይ በግብርናው ዘርፍ የተገኙ የተለያዩ ስኬቶችን የሚያሳዩ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች፣ ዲጂታላይዜሽንና የግብርና ፋይናንስ ላይ ያተኮሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

በዚህም የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ በተለያዩ የክፍል ደረጃ ያሉ ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም ጎብኝተዋል።

በዛሬው እለትም የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አመራርና ሠራተኞች አውደ-ርዕዩን ጎብኝተዋል።

የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት  የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ግርማ ወርቁ፤ በጉብኝቱ የግብርናውን ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ አስደናቂ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ተመልክተናል ብለዋል።

በከተማዋ የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት የተሳካ ለማድረግ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የማስተዋወቅ ሥራ እንሰራለን ነው ያሉት።

ከጉብኝቱ ታዳሚዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞች በአውደ-ርዕዩ በተመለከቱት መደነቃቸውን ጠቅሰው፤ በግብርና ዘርፍ አገሪቷ የጀመረቻቸው ሥራዎች ለስኬት እንደሚበቁም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

የግብርና የሚኒስትሩ አማካሪ ማርቆስ ሌራንጎ ፤ የኤግዚቢሽኑ መዘጋጀት ዋና ዓላማ የግብርናውን ዘርፍ ከኋላቀር አሠራር ለማላቀቅ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ለሳይንስ ውጤቶች ትኩረት እንዲሰጡ ለማስገንዘብ ነው ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የዘርፉን ባለድርሻ አካላት ጨምሮ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ኤግዚቢሽኑን እየጎበኙ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ቀናት ሌሎችም እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

ኤግዚቢሽኑ ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ከተደረገ ጀምሮ እስካሁን ከ45 ሺህ በላይ ዜጎች የጎበኙት መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም