ዩኒቨርሲቲው በ22 ሚሊዮን ብር  ወጪ ያስገነባውን የመኖ ማቀነባበሪያ ሥራ አስጀመረ

207

ደሴ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ) ፡- ወሎ ዩኒቨርሲቲ በአማራ ክልል አምስት ዞኖች ያለውን የእንስሳት መኖ እጥረት ለማቃለል በ22 ሚሊዮን ብር  ወጪ ያስገነባውን የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ሥራ አስጀመረ።

ማቀነባበሪያው በአማራ ክልል በደቡብና ሰሜን ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ ዋግ ኸምራ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች መኖን ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዝ ሲሆን፤ በቀን 360 ኩንታል መኖ የማምረት አቅም እንዳለውም ተገልጿል። 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ ማቀነባበሪያውን ሥራ ለማስጀመር ዛሬ በተዘጋጀ ሥነ ስርአት ላይ እንዳሉት፣ ተቋሙ ከመማር ማስተማርና ምርምር ባሻገር በማህበረሰብ አገልግሎት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው።

በዞኖቹ ያለውን የእንስሳት እርባታና ማድለብ ሥራ አጠናክሮ ለማስቀጠል ማነቆ የሆነውን የእንስሳት መኖ እጥረት ችግር ለማቃለል በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለእዚህም ዩኒቨርሲቲው በ22 ሚሊዮን ብር ያስገነባው የመኖ ማቀነባበሪያ ዛሬ ሥራ መጀመሩን ነው ፕሬዚዳንቱ ያስታወቁት።

እንደፕሬዚዳንቱ ገለጻ በቀጣይም ተጨማሪ የመኖ ማቀነባበሪያ በመገንባት ጥራት ያለው መኖ በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ይሰራል።

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ኃይሉ በበኩላቸው "በምንሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት የኅብረተሰቡን ችግር በጥናትና በምርምር ጭምር ታግዞ ለመፍታት እየሰራን ነው" ብለዋል።

በዞኖቹ ለእንስሳት ሀብት ልማት ያለውን ተስማሚነትና ተግዳሮት ለመለየት በተደረገ ጥረት የእንስሳት መኖ እጥረትና ጥራት መጓደል እንዳለ በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል።

በዚህም ለህብረተሰቡ መኖ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዩኒቨርሲቲው ማቀነባበሪያውን መገንባቱን ገልጸዋል። 

የመኖ ማቀነባበሪያው በቀን 360 ኩንታል መኖ እንደሚያመርት የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ሕክምና ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ታረቀኝ ትንታጉ ናቸው።

እንደ ዲኑ ገለጻ ማቀነባበሪያው በዋናነት ለከብቶች ማድለብ፣ ለወተት ላም፣ ለእንቁላል ጣይ ዶሮ እና ለዶሮ ጫጩት የሚሆን መኖ ያመርታል።

ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ለማድረስም ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና ሐይቅ ከተሞች ላይ የመኖ ማከፋፈያ ቅርንጫፎች እንደሚከፈቱ ዶክተር ታረቀኝ አስታውቀዋል።

በደሴ ከተማ በወተት ላም እርባታ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል ወጣት ይመር ዓሊ በሰጠው አስተያየት በአካባቢያቸው በቂና ጥራት ያለው መኖ ባለማግኘታቸው ላሞቹንና ጥጆቹን ለመመገብ ሲቸገር እንደነበር ገልጿል።

ዝርያቸው የተሻሻሉ ላሞችን ቢያረባም በመኖ እጥረት በሚፈለገው ልክ ወተት ለማግኘት እንዳልቻለ ገልጾ፣ በዩኒቨርሲቲው የተገነባው ማቀነባበሪያ ችግሩን ይፈታል የሚል እምነት እንዳደረበት ተናግሯል።

በማቀነባበሪያው ሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም