በወይዘሪት ፀጋ በላቸው ላይ ከተፈጸመው የጠለፋ ወንጀል ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

230

ሀዋሳ ግንቦት 22 / 2015 (ኢዜአ)፡-በሀዋሳ ከተማ በወይዘሪት ፀጋ በላቸው ላይ ከተፈጸመው የጠለፋ ወንጀል ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አስታወቀ።
 

የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር መልካሙ አየለ የከተማችን ነዋሪ በሆነችው ወይዘሪት ፀጋ በላቸው ላይ የደረሰባትን የጠለፋ ወንጀል ቤተሰቦቿ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ለፖሊስ አቤቱታ አቅርበዋል ብለዋል።

በዚህም የፖሊስ መምሪያው ተፈጸመ በተባለው የወንጀል ድርጊት መሰረት ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ብርቱ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሂደቱም የጸጥታ ሀይሉ ባደረገው ክትትል ከወይዘሪት ፀጋ በላቸው የጠለፋ ወንጀል ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ መጀመሩን አብራርተዋል።

የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ መምሪያው ከሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ጭምር አስፈላጊውን ጥረት እያደረገም እንደሚገኝ በመግለጫቸው አመላክተዋል። 

ሁሉም ሰው ከህግ በታች በመሆኑ የወንጀሉ ፈጻሚን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመላክተው፤ በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች በሚሰራጩ አሉባልታዎች ህብረተሰቡ መደናገር እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።

ህብረተሰቡ ፖሊስ የሚያደርገውን ክትትል መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የፀጥታ አካላትና ፖሊስ ተጠርጣሪው ሣጅን የኋላ መብራቴ እና የተጠለፈችውን ወይዘሪት ፀጋ በላቸው ይዞ ከተሰወረበት ቦታ አድኖ ለመያዝ የሚያደርገውን ጥረት ህብረተሰቡ እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

በመሆኑም 09 64 50 46 77 እና 09 69 41 52 72 ስልክ ቁጥሮች ህብረተሰቡ ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
 

የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ በበኩላቸው የጸጥታ ሀይሉ አቤቱታው ከደረሰበት ዕለት አንስቶ ወንጀሉን የፈጸመውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ለማዋል የተቀናጀ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይም ተጠርጣሪው ይኖርበታል ተብሎ በሚገመትባቸው ቦታዎች የጸጥታ ሀይል የተሰማራ መሆኑን ጠቁመው፤ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ተጠርጣሪው ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሸሽቶ በክልሉ የተሰወረባቸውን አካባቢዎችና ከአጎራባች ክልሎች የጸጥታ ሀይሎች ጋር የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ወንጀል ፈጻሚውን ግለሰብ በተቀናጀ መንገድ ከቁጥጥር ስር ለማዋል የጸጥታ ሀይል ያለዕረፍት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የሚደረገውን ጥረት ማህበረሰቡ እንዲደግፍ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም