የ2024 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ሉሲዎቹ በመጀመሪያ ዙር ከቻድ ጋር ተደልድለዋል - ኢዜአ አማርኛ
የ2024 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ሉሲዎቹ በመጀመሪያ ዙር ከቻድ ጋር ተደልድለዋል

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በፓሪስ በሚካሄደው የ2024 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዎች በመጀመሪያ ዙር ከቻድ ጋር መደልደሉ ታውቋል።
የኦሊምፒክ ውድድሩ ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ይከናወናል።
ዛሬ በወጣው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዎች ድልድል ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ዙር ከቻድ ጋር እንደምትጫወት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ሉሲዎቹ የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን ከሐምሌ 3 እስከ 11 ቀን 2015 ባሉት ቀናት እንደሚያደርጉ ገልጿል።
ብሔራዊ ቡድኑ በአጠቃላይ ውጤት ካሸነፈ በሁለተኛ ዙር ከናይጄሪያ አቻው ጋር የሚጫወት ይሆናል።
የ2024 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዎች በአራት ዙር እንደሚደረጉ ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።