በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን ለማስፈን በአምራች ኢንዱስትሪውና በግብዓት አቅራቢ መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር ይገባል- ተመራማሪ  ዶክተር ማርያማዊት ፍቅረስላሴ

161

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ) ፦  በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን ለማስፈን በአምራች ኢንዱስትሪውና በግብዓት አቅራቢ መካካል ያለው ትስስር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደርና የድህረ-ምረቃ አስተባባሪና ተመራማሪ  ዶክተር ማርያማዊት ፍቅረስላሴ ገለጹ።

በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የተገኘውን ዘርፈ ብዙ እመርታ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍም ለማምጣት ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።

ለዚህ ደግሞ ወሳኝ የሆነውን የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የፋይናንስ አቅርቦት በማረጋገጥ በኩል በተሻለ አቅጣጫ መጓዝ ተችሏል።

በኢንዱስትሪያላይዜሽን ዘርፉ በዋናነት የሚታየው የመሬትና የመስሪያ ቦታ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ክላስተሮችን የመፍጠር ተግባር በመከናወን ላይ ይገኛል። 

ለአብነትም በኢትዮጵያ ከሚገኙት  ነባር  12 የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተጨማሪ ላለፉት ስምንት ዓመታት በ88 ሄክታር መሬት ላይ ሲገነባ ቆይቶ የተጠናቀቀውንና ለአልሚ ባለሃብቶች ክፍት የሆነው የቦሌ ለሚ ቁጥር 2 እና የቂሊንጦ ማስፋፊያ ፕሮጀክትን ማንሳት ይቻላል፡፡

እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውም ይነገራል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደርና የድኅረ-ምረቃ አስተባባሪና ተመራማሪ  ዶክተር ማርያማዊት ፍቅረስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን ለማስፈን በአምራች ኢንዱስትሪውና በግብዓት አቅራቢ መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር ይገባል።

የግብርና ምርት የሚጠቀሙ፣ ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚቀጥሩ እንዲሁም የገቢ ተኪ ምርቶችና የውጭ ንግድ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ግብዓት አቅራቢ  ጋር ለማስተሳሰር  የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ግብርና እና ከግብርና ጋር ተያያዥ በሆኑ የንግድ ስራዎች(አግሪ ቢዝነስ) እንዲሁም ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥተው በመሰማራት በሁሉን አቀፍ የገበያ ትስስር ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የተጀመሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማልማትና የግል  ባለሃብቱ ወደ ዘርፉ እንዲገባ ማገዝ እንደሚገባና ይህም በፍጥነት እንዲሳካ የኢንዱስትሪ ልማት ከግብርና እና ከአገልግሎት ልማት ዘርፍ ጋር አዎንታዊ፣ ተመጣጣኝ የእድገት ደረጃን መሠረት ያደረገ  ትስስርን  መፍጠር እንደሚያስፈልግ ነው ተመራማሪዋ ያስረዱት።

በዓለም አቀፍ ያሉ ኢንዱስትሪዎች አንዱ ለሌላው የሚሆኑ እሴት የተጨመረባቸው ያለቁና በከፊል ያለቁ ጥሬ ግብዓቶችን በማምረት የእርስ በርስ ዘርፈ-ብዙ ትስስር በመፍጠር በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን አማራጭ የመከተል ልምድ አዋጭ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ልማት አነስተኛ መዋዕለ-ንዋይ የሚጠይቁና ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚቀጥሩ መሆን እንደሚገባቸው በማንሳት።

በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሰማሩ የውጭ አገር ባለሃብቶች በቀጥተኛ ምርት ማምረት ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ የክህሎትና የዕውቀት ሽግግር ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ማንኛውም አዳጊ አገር ለኢንዱስትሪ ልማት የሚያስፈልጉ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል አንፃራዊ ጥቅም በሚገኝባቸው ምርቶችና አገልግሎቶች ለዓለም አቀፍ ገበያ በማስፋት ማቅረብ ይገባል ነው ያሉት ዶክተር ማርያማዊት።

በተለይም በግብርና ግብርና ነክ ኢንዱስትሪዎች ለማዕድንና የቱሪዝም ዘርፍ እንዲተሳሰሩ ማድረግ እና 

የትምህርት ተቋማትም ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን የሰው ኃይል ማፍራት፣ የተቋማት ግንባታና የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ላይ በመመስረት ትስስሩን ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን አክለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም