የትራንስፖትና ሎጅስቲክስ ዘርፉን በማዘመን አገራዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው- ሚኒስቴሩ

111

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የትራንስፖትና ሎጅስቲክስ ዘርፉን በማዘመን አገራዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ፤ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዘርፉን ለማሳለጥ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። 

በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥ፣ ሀገራዊ የሎጅስቲክስ አገልግሎትን ለማስፋትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ስትራቴጂያዊ አሰራሮች መዘርጋታቸውን አብራርተዋል።

ለዘርፉ ውጤታማነት በሁሉም መልኩ አስቻይ አቅሞች እየተገነቡ መሆኑን ጠቅሰው የትራንስፖትና ሎጅስቲክስ አገልግሎቱን በማዘመን አገራዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም በባህርና በየብስ የትራንስፖርት መስኮች ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጡ አሰራሮች እንደነበሩ አስታውሰው አሁን ላይ ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችሉ በርካታ የመፍትሄ አመራጮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

በሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት የሚያሰችሉ ሁሉን አቀፍ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በተለይም 95 በመቶ የሚሆነው የወጪና ገቢ ንግድ የሚስተናገድበት የኢትዮ-ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪዶር ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጀመሩት ዘመናዊ አሰራሮች በወደብ ላይ የሚቆዩ ምርቶችን በተፋጠነ ሁኔታ ማንሳት አስችሏል ብለዋል።

የሎጅስቲክስ ዘርፉን ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚኖረውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ በተቀናጀ መልኩ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም