ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በውጤታማነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር ይገባል- ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ)፦ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በውጤታማነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በሚመለከት በአዲስ አበባ የተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን ለማስፋት የሚያስችል የልምድ ልውውጥ  ከአማራ ክልል ጋር አካሄዷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ፣የከተማ አስተዳደሩ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ተክሌ በዛብህ፣ የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ  ገረመው ገብረፃዲቅ  ጨምሮ  የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ መንግስት በመላው ኢትዮጵያ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጠናከረ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በዘርፉ ከሚሰሩ አጋር አካላት ጋር ''የትብብር ጥምረት'' ማቋቋሙን አመልክተዋል።

ጥምረቱ የከተማዋ ፍትህ ቢሮ በባለቤትነት የሚመራው ሲሆን በዘርፉ የተሰማሩ ዓለም አቀፍና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካተታቸውን ተናግረዋል።

የሰዎች ዝውውር በስፋት የሚታዩባቸው አካባቢዎችን በመለየት የቁጥጥርና የክትትል ስራዎች ማከናወን የጥምረቱ ዋነኛ ተግባር መሆኑን ነው ምክትል ከንቲባው ያስረዱት።

በዘርፉ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማስፋትና ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝና የትብብሩን ጥምረት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በማስፋት ወንጀሉን ማስቆምና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል።

ከአማራ ክልል ጋር የተደረገው የልምድ ልውውጥ የዚሁ አካል መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባው መሰል ተግባራትን ወደ ሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የማስቀጠል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም